ቀጥታ፡

የኢንዶኔዥያ አምባሳደር ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ደሴ ከተማ ገቡ

ህዳር 3/2012 በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡሽራ ባስኑር ለሦስት ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ደሴ ከተማ ገቡ። አምባሳደሩ ኮምቦልቻ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁንን ጨምሮ የኮምበልቻ ከተማ አመራሮችና ባለሃብቶች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ አምባሳደሩ ወደ ደሴ ከተማ የመጡት የወሎ ዩኒቨርሲቲን ከኢንዶኔዥያ አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር፣ የአገራቸውን ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከደሴና ኮምቦልቻ ባለሃብቶች ጋር ተባብረው የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው ተብሏል ። አምባሳደር አልቡሽራ በሦስት ቀን ቆይታቸውም ከወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ተማሪዎች ፣ ከደሴና ኮምቦልቻ ከተማ ባለሃብቶች ጋር በኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን እንደገለጹት አምባሳንደሩ ነገ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ተማሪዎች ጋር በቴክኖሎጂና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የአገራቸውን ልምድ ያጋራሉ ብለዋል፡፡ በኢንዶኔዥያ በርካታ ብሔር ብሄረሰቦችና የተለያዩ ቋንቋዎች እንዴት ተቻችለው በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት እንደሚኖሩ ተሞክሮ በማስተላለፍ ልዩነት ጌጥና ውበት መሆኑን ለተማሪዎች ማብራሪያ እንደሚሰጡ ገልፀዋል። አምባሳደር አልቡሽራ በሐምሌ ወር 2011ዓም  ከደሴ ከተማ ባለሃብቶች፣ አመራሮችና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረጉት ውይይት በጋራ ለመስራት ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው ፡፡ በቃላቸው መሰረትም ከ20 በላይ የደሴ ከተማ ባለሃብቶች ኢንዶኔዥያ ሔደው የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ማድረጋቸውንና 10 የሚሆኑ የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች ደሴና ኮምቦልቻ ላይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ሁኔታዎች ማመቻቸታቸውን  ተገልጸል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም