ቀጥታ፡

በአለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የባህል አልባሳት ምርት ማምረት አልተቻለም- አምራቾች

ህዳር 2/2012 በጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ምክንያት በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የባህል አልባሳት ምርት ማምረት እንዳልቻሉ አምራቾች ተናገሩ። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከባህል ልብስ አምራቾችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር  የዕደ ጥበብ ማበልፀግ ቡድን መሪ አቶ ጀማል አህመድ አምራቾች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲያመርቱ በቂ የሆነ አቅርቦት ማግኘት አለባቸው ብለዋል። ይህ ባለመሟላቱም የአገራችን ባህል አልባሳት በውጭ ምርቶች ተወረዋል። ይህንን ችግር ለመከላከልም በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች በቂ የግብዓት አቅርቦት እንዲያገኙ ማድረግ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል መፍጠርና ደረጃውን የጠበቀ የመሣሪያ አቅርቦት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ለአምራቾች ተገቢ የሆነ ድጋፍ በማድረግ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በማምረት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል እንደሚጠበቅም ነው ያስገነዘቡት። በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ  ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ቡድን መሪው፤ የገበያ ትስስር እንዲኖርና  በታችኛው ደረጃ ያሉ አምራቾች በሰሩት ስራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ነጋዴዎች የማይገባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ የቁጥጥር ስርዓቱ ጠንካራ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት በትብብር እየተሰራ እንደሆነም ነው አቶ ጀማል የተናገሩት። አምራቾች በቂ አቅርቦት አግኝተው የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ  ሁሉም የሚመለከታቸው  ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ለዘርፉ  ተገቢ የሆነ ድጋፍ ካልተደረገ አምራቾች ከገበያ ውጭ ይሆናሉ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ማንነታችንን የሚገልፁ ባህሎቻችንና እሴቶቻችንን እናጣለን ብለዋል ። ከባህርዳር ከመጡት የውይይቱ ተሳታፊ አምራች  አቶ ጀማል አወል ለኢዜአ እንደገለፁት በቂ የጥሬ ምርት አቅርቦት ባለመኖሩ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዳያመርቱ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል። በቂ የግብዓት አቅርቦት፣ የታችኛውን አምራች ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ቢዘረጋና ጠንካራ ድጋፍና ቁጥጥር ቢደረግ  በቀጣይ በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ማምረት እንደሚችሉ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የሚመረቱ ምርቶች በውድ ዋጋ የሚሸጡት ምርቱን ለማምረት ከውጭ አገር የሚገቡ ጥሬ እቃዎች በውድ ዋጋ በመግባታቸው ምክንያት እንደሆነም ገልፀዋል። ይህንኑ ሃሳብ የሚጋሩት ከትግራይ ክልል የመጡ አምራች  አቶ አወል ዘይኑ በበኩላቸው በቂ የግብት አቅርቦት የለም፣  በምናመርተው ምርትም ተጠቃሚ አልሆንም፤ ተጠቃሚዎቹ ከአምራቾች የሚቀበሉ ነጋዴዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች የሚመለከታቸው አካላት በቂ የሆነ ድጋፍ እንዲያደርጉና በሚያመርቱት ምርት ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም