ለቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ መስጠት የሚያስችል የህግና የቁጥጥር ማዕቀፍ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ለቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ መስጠት የሚያስችል የህግና የቁጥጥር ማዕቀፍ ተዘጋጀ
ህዳር 2/2012 ወደ ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለሚገቡ ኩባንያዎች ፈቃድ የመስጠቱ ሂደት እስከ 2012 ሶስተኛ ሩብ ዓመት ድረስ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ለፈቃድ አሰጣጡ የሚያግዘውን የህግና የቁጥጥር ማዕቀፍ አዘጋጅቷል። በኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ በውድድር ላይ የተመሰረተ አገልግሎት እንዲኖር ከአንድ ዓመት በፊት በመንግሥት በተሰጠው ውሳኔ መሰረት የግል ኩባንያዎችን በከፊል የማስገባት ስራ ተጀምሯል። ውሳኔው የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የቴሌኮም አገልግሎትን በውድድርና በጥራት መስጠትን ዓላማ ያደረገው የመንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ አካል ነው። ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ፣ ነጻና ገለልተኛ በሆነ መልኩ በከፊል ወደ ግል የማዘዋወር ሂደቱን ለማስፈፀም የኮሙኒኬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን መቋቋሙ ይታወሳል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ መሠረት በግልጽ ውድድር ሁለት ተጨማሪ አዲስ ፈቃዶችን ለቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኦፕሬተሮች ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል። ፈቃድ የመስጠት ሂደቱም በ2012 ሶስተኛ ሩብ ዓመት ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ መሰረት ባለስልጣኑ ለግል ኩባንያዎቹ ፈቃድ መስጠት የሚያስችለውን የህግና የቁጥጥር ማዕቀፍ አዘጋጅቶ በዘርፉ የመሰማራት ፍላጎት ካላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ጋር ውይይት አድርጓል። ማዕቀፉ እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ለማመቻቸት የቁጥጥር ስራውንም የተቀላጠፈ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት በጥንቃቄ እንደተዘጋጀም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የውይይት መድረኩ እስከ ህዳር 22 ቀን 2012 ዓ ም የሚቀጥል ሲሆን ማዕቀፉ ግልጽና አሳታፊ እንዲሆን በየደረጃው ያሉ የዘርፉ ተዋንያን የሚሳተፉበትና ግብዓት የሚሰበሰብበት ነው ብለዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ መንግስት ባለፉት 10 ዓመታትያስመዘገበውን ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል በተለይ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ቀርጾ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ለውጦች ማምጣት ቢቻልም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት፣ የወጣቶች ስራ አጥነት እንዲሁም የግል ዘርፉ ተሳትፎ አነስተኛ መሆን የኢኮኖሚ ዕድገቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይቀጥል ማድረጉን አብራርተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግስት በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ እያደረገ ያለው ማሻሻያ ጥራትና ቀጣይነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የግል ዘርፉን በስፋት ማሳተፍ ላይ ቁርጠኛ አቋም ይዟል። በዚህም የማክሮ ኢኮሚውን መዛባት በፍጥነት በማስተካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረትን መፍታት የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት። ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት መንግስት የቴሌኮም ዘርፉ ላይ የጀመረውን ማሻሻያ በማፋጠን በቅርቡ ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል። የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ለማድረግ አስተማማኝ ኢኮኖሚ የመገንባት ስራ ተጀምሯል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 ነሃሴ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተወዳዳሪ የገበያ ሥርዓትን በማበረታታት የተጠቃሚዎችን ተደራሽነትና ፍላጎት ያሟላ ጥራቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ያገናዘበ የኮሙኒኬሽንና የፖስታ አገልግሎት በመላ አገሪቱ ማስፋፋትን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ነው።