ቀጥታ፡

ፌዴሬሽኑ በጥሎ ማለፍ ውድድር የመርሃ ግብር ማስተካካያ አደረገ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ላይ የመርሃ ግብር ማስተካከያ ማድረጉን አስታወቀ። በዚህም መሰረት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት መከላከያ ከድሬዳዋ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ነገ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት የሚካሄድ ይሆናል። በተመሳሳይ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ከ30 ኢትዮ ኤሌትሪክና መቐለ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ነገ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት እንደሚካሄድ ታውቋል። ነገ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማና ሲዳማ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ የሃዋሳ ከተማ ክለብ በጊዜያዊነት በመበተኑ ምክንያት ክለቡ ጨዋታው ለሌላ ጊዜ ይራዘምልኝ በሚል ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ጨዋታው ሌላ ጊዜ እንደሚካሄድ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ነገ በአርባምንጭ ስታዲየም አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 11 ከ30 ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄድ ተገልጿል። ደደቢት ከጥሎ ማለፍ ውድድሩ ራሱን በማግለሉ ምክንያት የጅማ አባጅፋርና የደደቢት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የመካሄድ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ሚያዚያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን፣ ፋሲል ከተማ አዳማ ከተማን እና ኢትዮጵያ ቡና ወልዲያ ከተማን በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፋቸው የሚታወስ ነው። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ የሚሆነው ቡድን በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ይሳተፋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም