ቀጥታ፡

የማምረቻ ዘርፉን ምርታማነት ለማሻሻል የሚያስችል ስልጠና ሊሰጥ ነው

ህዳር 2/2012 በማምረቻ ዘርፉ የተሰማራውን የሰው ኃይል የምርታማነት አቅም ለማሻሻል የሚያስችል አገር አቀፍ ስልጠና በቅርቡ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ስልጠናው የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ዕርዳታና ከኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ጋር በትብብር የሚሰጥ ነው። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ እንደተናገሩት በማምረቻው ዘርፍ የተሰማራው የሰው ኃይል በአብዛኛው ከገጠሪቱ የአገሪቷ ክፍል የሚመጣ በመሆኑ ዘመናዊ የምርት ሂደት ልምድ ችግር ይስተዋልበታል። በፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ አዳዲስ ሰራተኞች የሚጠበቅባቸውን የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ታዲያ ስልጠናው የኢንዱስትሪ ትውውቅ ለመፍጠርና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። ስልጠናው በምስልና በድምጽ የተደገፈ በመሆኑም ይህ ዓይነት ስልጠና በዘርፉ ለተሰማራው የሰው ኃይል ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም ጠቁመዋል። እንዲሁም ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ፍላጎት በሰለጠነ ባለሙያ ለማሟላት ስልጠናው የነቃና አምራች የሆነን የሰው ኃይል ለመገንባት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ከአጋር አካላት ጋር የሚሰጡ ስልጠናዎች በኢንዱስትሪው ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ናቸው። ለአብነትም በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ተቀጥረው ለሚሰሩ ሰራተኞች በተሰጠ ስልጠና የምርታማነት ዕድገት መታየቱን አቶ ስለሺ  ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከተገኘው ገቢ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው ምርት ከሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ መሆኑን በማመላከት። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሀና አርአያስላሴ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የማምረቻውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሻሻልና አገሪቷ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ መሰል ስልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል። በኢንዱስትሪያል ፓርኮች ውስጥ የተሰማራውን የሰው ኃይል አቅም ለማጎልበት ከጃፓን፣ ከጀርመንና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። በእንግሊዝ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የተቋቋመው የኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የፕሮግራምና የፓርተነርሺፕ ኃላፊ ሚስተር ነቢል ኬሎው በበኩላቸው በኢትዮጵያ በአግሮ ኢንዱስትሪና በፋይናንስ ዘርፎች የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ ድርጅታቸው በአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ መሰማራቱን ገልጸዋል። በቅርቡ በማምረቻ ዘርፉ የተሰማራውን የሰው ኃይል የምርታማነት አቅም ለማሻሻል በሚጀመረው አገር አቀፍ ስልጠናም 100 ሺህ ሰራተኞች እንደሚሳተፉም አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም