ቀጥታ፡

የሳምባ ምች በሽታን ለመከላከል መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ ተጠየቀ

ኅዳር  2 ቀን 2012 የህጻናት አድን ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስትንና የሚመለከታቸውን አካላት የልጆችን ህይወት እየቀጠፈ ላለው የሳምባ ምች በሽታ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ሲል ጥሪ አቅርቧል። ድርጅቱ የሳምባ ምች በህጻናት ህይወት  የሚያደርሰውን  ጉዳት  ላይ  አስመልክቶ ያደረገውን የጥናት መግለጫ ሰጥቷል። የሳምባ ምች በሽታ በባክቴሪያ፣ በቫይረስ ወይም በፈንገስ የሚመጣ ሆኖ የህጻናት ሳምባን በፈሳሽ ሞልቶ በአተነፋፈሳቸው ላይ ችግር በመፍጠር ለሞት የሚዳርግ ነው። በተለይም በሽታን የመከላከል አቅም በቀነሰባቸው፣ የተበከለ አየርና ንጹህ ውሃ በሌለበት አካባቢ ህጻናት ተጋላጭ መሆናቸውን የገለጸው መግለጫው፤ በአገራችንም ለአብነት    5 ዓመት ካልሞላቸው ህጻናት ተጋላጭነት ከአዲስ አበባ  ከአፋር ክልል  በ3 እጥፍ ይበልጣል ተብሏል። ችግሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባሉ ቤተሰብ በተወለዱ ህጻናት እንደሚከፋና በመሞት ዕድላቸውም ከተሻለ ኑሮ ቤተሰብ ከተወለዱት ጋር ሲነጻጸርም በ30 በመቶ የሰፋ መሆኑን ገልጿል። ከበሽታው ጋር የተገናኙ ሞቶችን በቀላል ክትባት ወይም በአነስተኛ ህክምና አገልግሎት ማስቀረት እንደሚቻል ያነሳው መግለጫው፤ ከሶስት ህጻናት ሁለቱ ያንን በቂ የህክምና እርዳታ በወቅቱ አያገኙም ብሏል። በድርጅቱ የጤናና የስነ-ምግብ ፕሮግራሞች ሃላፊ ዶክተር ዘላለም ሐብታሙ በሽታውን ለማስቆም የሚደረገውን ርብርብ መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠትና አገራዊ ስትራቴጂን በመንደፍ የመከላከልና የቁጥጥር ስራ እንዲሰራ አሳስበዋል። በሽታው ባለፈው ዓመት ብቻ 17 በመቶ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ህይወት መቅጠፉን ያስታወቀው መግለጫው በየሰዓቱ አገሪቱን የ4 ልጆችን ህይወት  እያሳጣ መሆኑንም ጥናቱ ማመላከቱ ተጠቁሟል። እንዲሁም ባለፈው ዓመት ብቻ በተመሳሳይ ዕድሜ ያሉ ለ32 ሺህ ህጻናት ሞት ምክንያት ነው ያለውን የጥናት ግኝት በማስረጃነት ጠቅሶ ድርጅቱና መንግስት በሽታውን ለማስቆም ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስዱ  ጥሪ አቅርቧል። ስለ በሽታው አስከፊነት የዓለም መረጃም እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት በወባ ምክንያት ከሞቱት 272 ሺህ እና በአጣዳፊ ተቅማጥ ከሞቱት 437 ሺህ ህጻናት ጋር ሲነጻጸር በሳምባ ምች የሞቱት 802 ሺህ በማድረስ በገዳይነቱ ቁጥር አንድ አድርጎታል። እ.አ.አ በ2018 ከተመዘገቡት የሳምባ ምች ሞት አሃዞች በዓለም አገራት የፊተኞቹ ናይጄሪያ 162,000፣ ህንድ 127,000፣ ፓክስታን 58,000፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ 40,000 እንዲሁም ኢትዮጵያ 32,000 መሆናቸውን መግለጫው ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም