በሁመራ ከተማ ከአራት ኩንታል በላይ አደንዛዥ እጽ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በሁመራ ከተማ ከአራት ኩንታል በላይ አደንዛዥ እጽ ተገኘ
ሁመራ 2/2012 ፡- በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ሁመራ ከተማ በህገወጥ መንገድ በተሽከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረ ጋንጃ የተባለ አደንዛዥ ዕፅ መገኘቱን በኢትዮጰያ ጉምሩክ ባለስልጣን የሁመራ መቅረጫ ጣቢያ አስታወቀ፡፡ የጣቢያው ስራ አስኪያጅ ኮማንደር መለሰ ይመም ለኢዜአ እንደገለጹት በአዘዋዋሪዎች ሲጓገዝ የደረሱበት አደንዛዥ እጹ መነሻው ከየት አካባቢ እንደሆነ ለጊዜው በውል አልታወቀም። 474 ኪሎ ግራም የሚመዘነው "ጋንጃ" አደንዛዥ እጽ የተገኘው በሁመራ ከተማ ቀበሌ አራት ልዩ ቦታው እንዳ ጀወርግስ በሚባል አካባቢ ነው። በአካባቢው የፀጥታ አካላትና የጣቢያው ሰራተኞች በትብብር ባደረጉት ክትትል ወደ ሌላ ሀገር ለማስወጣት አስራ ኪሎ ሜትር ሲቀረው በአዘዋዋሪዎች ተሸሸጎ ማግኘታቸውን ኮማንደሩ ተናግረዋል። እጹን ጭኖ የተገኘው ተሽከርካሪ የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 - 46 686 አዲስ አበባ የሆነ አይሱዙ ነው። አዟዋዋሪዎቹ እጹንና የጫነው ተሽከርካሪ ጥለው ለጊዜው ቢሰወሩም ለመያዝ የጸጥታ አካላት ክትትል እያደረጉባቸው ይገኛል። ስራ አስኪያጁ እንዳመለከቱት አዟዋዋሪዎቹ እጹ እንዳይታወቅባቸው በአስራ ሁለት ከረጢት ቋጥረው ዙሪያው ደግሞ በጤፍና የምግብ ዘይት ከልለው ለማሳለፍ ነበር፡፡