የሀሮ ቡራ የመጠጥ ውሃ ግድብ ለአገልግሎት ተዘጋጀ

ነገሌ ኢዜአ ህዳር 2/2012 በቦረና ዞን በ10 ሚሊዮን ብር ማስፋፊያና እድሳት የተደረገለት የሀሮ ቡራ የመጠጥ ውሃ ግድብ ለአገልግሎት መዘጋጀቱን የኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደር ኮሚሽን ገለጸ፡፡ የግድቡ አካባቢ ነዋሪዎች ለግድቡ እንክብካቤና ጥበቃ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ መሐመድ ጂሎ የአራት ወረዳዎችን ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርገው ግድቡ ከጥር ጀምሮ አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው። ግድቡ ሥራ የሚጀምረው ከ11 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚበልጥ የዝናብና የጎርፍ ውሃ በማጠራቀም መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ ግድቡ ከሚይዘው የውሃ መጠን 80 በመቶ ውሃ መጠራቀሙን ገልጸዋል፡፡ ለአርብቶ አደሩ ማህረሰብ ክረምት ከበጋ አገልግሎት የሚሰጠው ግድብ 400 ሄክታር ስፋትና አምስት ሜትር ጥልቀት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ግድቡ ለ10 ሺህ ሕዝብና 5 ሺህ የቤት እንስሳትን በየቀኑ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡ ግድቡ የመስኖ ልማትና የዓሳ ርባታ ፕሮጀክቶች እንደሚካሄድበት አስታውቀዋል፡፡ የአርብቶ አደሩን ችግር ለመፍታት በዚህ ዓመት የተጨማሪ ግድቦች ግንባታና ጥልቅ የመጠጥ ውሀ ጉድጓዶች ቁፋሮ እንደሚከናወን አቶ መሐመድ ጠቁመዋል፡፡ የኤሎያ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጉራ ገልገሎ ግድቡ የመጠጥ ውሃ ችግራቸውን ስለሚያቃልል መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚሀም ለሰውና ለቤት እንስሳት ውሃ ፍለጋ ይገጥማቸው የነበረው መንከራተት እንደሚያስቀርላቸው ተናግረዋል፡፡ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ከአካባቢያቸው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ችግኝ በመትከልና እርከን በመስራት እንደሚንከባከቡት ገልጸዋል፡፡ የዚሁ ወረዳ ሌላው ነዋሪ አቶ ሁሴን ታሪ ግድቡ ባለፉት ዓመታት ይገጥማቸው የነበረው የውሃ ችግር እንዳይከሰት ስለሚያደርግ እንክብካቤና ጥበቃ እንደሚያደርጉለት አስታውቀዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም