ደቡብ ኮሪያ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የኮሪያ ዘማቾች መርጃ ማዕከል ገነባች - ኢዜአ አማርኛ
ደቡብ ኮሪያ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የኮሪያ ዘማቾች መርጃ ማዕከል ገነባች
ህዳር 2/2012 ደቡብ ኮሪያ ከአፍሪካ ሀገር በብቸኝነት ለኮርያ ጦርንት ለዘመቱ ኢትዮጵያዊያን የመርጃ ማዕከል መገንባቷን የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትር መግለፃቸውን የደቡብ ኮሪያ የዜና አውታር ዘግቧል። እንደ መከላከያ ሚኒስተሩ ገለፃ በአዲስ አበባ የተገነባው የመርጃ ማዕከል 712.8 ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን የግንባታው ወጪ የተሸፈነው በደቡብ ኮሪያው ሎተ ግሩብ እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል። እ.ኤ.አ. ከ1950 እስከ 53 ለነበረው ግጭት ኢትዮጵያ ወታደሮችን በመላክ ከአፍሪካ ብቸኛ ሀገር ስትሆን ከተላኩት 3ሺ500 ወታደሮች መካከል 122 ሲሞቱ 536 ደግሞ በሶስት ዓመታት ግጭት ውስጥ ቆስለዋል አሁን ላይ ወደ 150 የሚጠጉ ዘማቾች በህይዎት እንደሚገኙ በመረጃው ተጠቅሷል። በኢትዮጵያ የተገነባው ይሄው የመርጃ ማዕከል ደቡብ ኮሪያ ለአለም አቀፉ ወታደሮች ቁርጠኝነት መስዋትነት ምስጋናና አክብሮት ለመስጠት ከያዘቻቸው ሶስት ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ተብሏል። ይህ ጉዳይ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ጥሩ እድል ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እንዳወቅ አብጤ በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ ተናግረዋል። እንደ ደቡብ ኮሪያ መንግስት መረጃ በኮሪያ ጦርነት ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ የተባበሩት መንግስታት ወታደሮች 3ሺ የጤና ባለሙያዎች የሰሜን ኮሪያን እና የቻይናን ወታደሮች ለመዋጋት ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር ከተሳተፉት ወስጥ 40ሺ670 የሚሆኑት ሲሞቱ 104ሺ280 ቆስለዋል ፡፡ በተጨማሪም ከ9 በላይ ወታደሮች የገቡበት እንዳልታወቀ የደቡብ ኮሪያ የዜና አውታር በዘገባው አውስቷል።