በጎንደር ዙሪያ በመጠለያ የቆዩ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመለሱ

63
ጎንደር  ህዳር 1 / 2012 ---ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የቆዩ ከ7 ሺህ በላይ አባውራዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደነበሩበት ቦታ ተመለሱ። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ መብራቱ ደጉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት ቀዬ መመለስ የተቻለው  የአካባቢው ሰላም ቀድሞ ወደ ነበረበት በመመለሱ ነው። "በዚህም ጎንደር ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ የነበሩትን ከ7ሺህ በለይ ተፋናቃዮች በወረዳው ማጫ አምቦ በር፣ ዳዋ ዳሞት፣ ሰርጉልትና ብርቧክስ ወደ ተባሉት ቀበሌዎች እንዲመለሱ ተደርጓል" ብለዋል፡፡ በዚህ ሳምንት ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው ለተለመሱት የወረዳው ተፈናቃዮችም 1ሺህ 565 ኩንታል የምግብ እህል፣ 1ሺህ 369 ሊትር የምግብ ዘይትና 15 ኩንታል አልሚ ምግብ መከፋፋሉን አመልክተዋል፡፡ አቶ ምብራቱ እንዳሉት ከእዚህ በተጨማሪ በግጭቱ መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው አባውራዎች 172 ጊዜያዊ የመጠለያ ድንኳን በነፍስ ወከፍ ተሰራጭቷል፡፡ ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራ የጀመሩ ሲሆን ለሰብል ስብሰባው የሚያግዝ ከ5ሺህ በላይ ማጭድ በዚህ ሳምንት እንደሚቀርብላቸውም አመልክተዋል፡፡ የተፈናቃዮችን የደረሱ ሰብሎች በመሰብሰብ ረገድ የ33ኛ ክፍለ ጦር የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በአምቦ በር ቀበሌ በመገኘት እገዛ ማድረጋቸውን አቶ መብራቱ ተናግረዋል፡፡ በዞን ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ተፈናቃዮችን ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን በተለይ መኖሪያ ቤታቸው የተቃጠለባቸውን አባውራዎች ቤት መልሶ ለመገንባት በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም