ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ በምስራቅ አፍሪካ ተጠቃሽ ተቋም ለመሆን እየሰራ ነው

ህዳር 1/2012፡- የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በምስራቅ አፍሪካ ተጠቃሽ ተቋም ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገለጸ። ኢንስቲትዩቱ ከሶማሊያ የመንግስሥት ሰራተኞች፣ ኃላፊዎች እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት 'ዩ ኤን ሀቢታት' የተውጣጡ ሰልጣኞችን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እያሰለጠነ ነው። ለስድስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ስልጠና 20 ሰልጣኞች እየተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው ፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ከተማ ፋይናንስና ከተማ ልማት ላይ ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚያግዝ ነውም ተብሏል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አታክልት ሀጎስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ የስልጠና አድማሱን ለማስፋት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ተቋሙ በውስጡ ያለውን የስልጠና ጥራት ለማሻሻል የማሻሻያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የሚተገበር የ15 ዓመት የትራንፎርሜሽን እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። እቅዱ ተቋሙ ከቆይታው አኳያ የት ነው ያለው? የሚሰጠው አገልግሎትስ ምን መሆን አለበት? ከአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት አንጻርስ የት መድረስ አለበት? የሚለውን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ዶክተር አታክልት ገለጻ ኢንስቲትዩቱ ከአገሪቷ አልፎ በአፍሪካም ተወዳዳሪ የስልጠና ተቋም ለመሆን የሰው ኃይል ማጠናከር ላይም በሚቀጥሉት ዓመታት ተከታታይነት ያለው ስራ ይሰራል። ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጪ ከሶማሊያ ለመጡ ሰልጣኞች የሚሰጠው ስልጠና በአገራቱ መካከል ያለውን ትስስር ከማጎልበት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይም የራሱን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም አክለዋል። ስልጠናው ተቋሙ ከአገሪቷ በሻገር የስልጠና አድማሱን ወደ ሌሎች አገራት ለማስፋት ለሚያደርገው ጥረት ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህም የሕዝብ ለሕዝብ ግኝኑነት እንደሚያጠናክር እምነታቸውን ገልጸዋል። ተቋሙ በምስራቅ አፍሪካ የሚሰጠውን ስልጠና ለማስፋፋት ከተለያዩ አገራት ጋር የአጋርነት ስምምነት እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመው ስምምነት ከሚደረስባቸው አገራት ጋርም ተቋሙ የሚሰጠውን ስልጠና ይቀጥላል ሲሉም አብራርተዋል። ከስልጠናው ተሳታፊ አንዱ አብዱልሀኪም ዑስማን በሰጠው አስተያየት ''ለስድስት ቀናት በኢትዮጵያ ስልጠና ለመውሰወድ በመምጣታችን እጅግ ደስተኞች ነን፤ በሚኖረን ቆይታም ለሕዝቡ አገልግልሎት የምንሰጥበትን አቅም እንደምናጎለብት ተስፋ አለኝ'' ብሏል። በተለይም ደግሞ ስልጠናው ከንድፈ ሀሳብ በተጓዳኝ የመስክ ምልከታንም የካተተ መሆኑ ሰፊ ልምድ የምናገኝበት ይሆናል ሲልም ተደምጧል። አሻ አህመድ ከሱማሌ ላንድ ሀርጌሳ መምጣታቸውን ያጫወቱን ሲሆን ከስልጠናው "የተሻለ እውቀት እንጠብቃለን" የሚል ሀሳብ አላቸው። ሰልጣኞቹ አዲስ አበባ ከቤት ልማት ጋር በተገናኘ የደረሰችበትን ደረጃ ተዘዋውረው እንደሚጎበኙም የወጣው መርሃ ግብር ይጠቁሟል። የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከተቋቋመ 61 ዓመት ሆኖታል።                                                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም