የክልሉን ሰላም በማጠናከር ልማትና መልካም አስተዳደርን ስኬታማ ማድረግ ይገባል---አቶ ርስቱ ይርዳው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ሰላም በማጠናከር ልማትና መልካም አስተዳደርን ስኬታማ ማድረግ ይገባል---አቶ ርስቱ ይርዳው
ሃዋሳ (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም---በደቡብ ክልል የመጣውን አንጻራዊ ሰላም በማጠናከር የተጀመሩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎችን ስኬታማ ማድረግ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ። በክልሉ ባለፈው ዓመት ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት 300 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል። ቢሮው ሴክተር ጉባኤውን ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ሲያካሂድ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት፣ በጸጥታ ችግር ምክንያት ዓምና ታቅደው ያልተከናወኑ ስራዎች አሉ። ዘንድሮ ያልተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጭምር ለማካካስ በሚያስችል መለኩ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ክልሉ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፉን ያስታወሱት አቶ ርስቱ፣ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የበርካታ ወገኖቻችን ህይወት ማለፉን አስታውሰዋል። "በጸጥታ ቸግሩ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ ንብረትም ወድሟል፤ በርካቶችም ከመኖሪያ ቄያቸው ተፈናቅለዋል” ብለዋል። በተለይ አምና ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በክልሉ መልካም ገጽታና ስም ላይ መጥፎ ጥላ ከማጥላት ባለፈ ክልሉ ማግኘት የሚገባውን ገቢና ጥቅም እንዳሳጣው አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ የመጣውን አንጻራዊ ሰላም በማጠናከር በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎችን ከግብ ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣው የህዝብ ጥያቄ ተገቢ ወዳልሆነ አቅጣጫ እንዳያመራ አቅም በፈቀደ መልኩ ፈጥኖ ለመፍታት በትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። "አምና ያልተፈጸሙ ዕቅዶችን ጭምር ለማካካስ መስራት ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል። አቶ ርስቱ እንዳሉት ፖሊስና የጸጥታ ኃይሉ በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቢኖርም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ፖሊስ ወገንተኛ በመሆን የህዝብን ሰላም የማስጠበቅ ተልዕኮውን እንዳልተወጣ ተናግረዋል። ችግሩን በመፍታት ለህዝቡ ሰላምና ጸጥታ የሚሰራ የፖሊስ ኃይል የመፍጠር ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዋል። የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዴ በበኩላቸው የግጭት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን መለየትና የሰላም እሴት ግንባታን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። አምና በአመራሩ መርህ አልባ እንቅስቃሴ ክልሉ የጸጥታ ችግር ውስጥ ገብቶ መቆየቱን አስታውሰው ለዘመናት የቆየው የክልሉ ብሄር ብሄረሰቦች አንድነት ችግሩ ጉዳት ሳያደርስ በአጭሩ እንዲቋጭ ማድረጉን ገልጸዋል። "በቀጣይ አመራሩ የህዝብን ፍላጎት በማርካትና ያልተፈቱ ጥያቄዎችን ለይቶ በመፍታት ዳግም ክልሉ ወደ ስጋት እንዳይገባ ማድረግ ይኖርበታል" ብለዋል። እን አቶ አለማየሁ ገለጻ በክልሉ ለግጭት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመለየት ጥናት እየተካሄደ ሲሆን በሚገኘው ውጤት መሰረት ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ይሰራሉ። በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙንና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘም ከተጠረጠሩ 1ሺህ 341 ሰዎች ውስጥ 929 ተይዘው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ሲሆን በመንግስትና በህዝብ ኃላፊነት ላይ ሆነው በወንጀል ከሚፈለጉ 129 አመራሮች ውስጥ 117ቱ ተይዘዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሴክተር ጉባኤ የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2012 ዕቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ታውቋል።