የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 54 ተርባይኖች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 54 ተርባይኖች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም
መቀሌ (ኢዜአ) ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም---በትግራይ ክልል የሚገኘው የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 54 ተርባይኖች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ ተገለጸ። የአሸጎዳ ነፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ብሩክ ኤባ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኃይል ያመነጩ ከነበሩ 84 ተርባይኖች መካከል በአሁኑ ወቅት 54ቱ ማመንጨት አቁመዋል። ብዙዎቹ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች አገልግሎት መስጠት ያልቻሉት በመለዋወጫ እቃዎች እጥረት መሆኑንም ጠቁመዋል። ''ቨርጅኔት ኤፍኤ" እና "አንስቶል ጂኢ'' የተባሉ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ተርባይኖቹን በአምስት ዓመት ውስጥ ጠግነው እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 ለማስረከብ ውል ቢወስዱም በአገር አቀፍ ደረጃ አጋጥሞ በነበረ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሥረውን መስራት እንዳልቻሉ አስረድተዋል። ሁለቱም ኩባንያዎች እስከ መስከረም 2017 ድረስ በሥራ ላይ እንደነበሩ ያስታወሱት ኢንጂነር ብሩክ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ክፍያ አለመፈጸሙ ስራውን እንዲያቋርጡ ማድረጉን አስታውሰዋል። በተደረገው ድርድር ''ቬርጅኔት ኤፍኤ'' የተባለው ካምፓኒ ተመልሶ ወደስራው ቢገባም ዳግም ክፍያ ባለመፈጸሙ ከሁለት ወር በፊት ስራውን ማቃረጡን ተናግረዋል። "በዚህም የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫው ለአምስት ወራት ያህል ሙሉ ለሙሉ ኃይል ማመንጨቱን አቋርጦ ነበር" ሲሉ ኢንጂነር ብሩክ ገልጸዋል። እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ከሚያዚያ 2018 ጀምሮ ደግሞ በተቋሙ አቅም ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ኢንጅነር ብሩክ፣ አሁንም የመለዋወጫ እቃዎች እጥረት ችግር እንደሆነባቸው ተናግረዋል። እንደሥራ አስኪያጁ ገለጻ ''አንስቶል ጂኢ'' በተባለው ካምፓኒ ተይዘው ከነበሩት 54 ተርባይኖች መካከል 30ዎቹ ተጠግነው አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆኑ ቀሪ 24 ተርባይኖች በጥገና ላይ ናቸው። ቬርጅኔት ኤፍ ኤ በተባለው ኩባንያ ተይዘው የነበሩ 30 ተርባይኖች በመለዋወጫ እቃዎች እጥረት ምክንያት ለሁለት ዓመት ያህል ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል። "ለተርባይኖቹ የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎች ከተሟሉ በተቋሙ ሠራተኞ አቅም ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ይሰራል" ብለዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው፣ በማመንጫ ጣቢያው የገጠመው ችግር በዋናነት ቴክንካል መሆኑን ገልጸው፣ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የመለዋወጫ እቃዎች ችግርን ለመፍታት ለሁሉም የነፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚያገለግል ግዢ እየተከናወነ ነው ብለዋል አቶ ሞጎስ። በተለይ አገርው ውስጥ የሚገኙትን ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር ውል ተፈፅሞ ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። "ከውጭ ሃገር የሚመጡ የመለዋወጫ እቃዎች ግዢ ለማከናወንም በግዥ ሂደት ላይ ነን" ብለዋል። የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ካሉት 84 ተርባይኖች 54ቱ እያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለቸው ታውቋል። ቀሪዎቹ 30 ተሪባይኖች ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው መሆኑን አቶ ሞጎስ ጨምሮው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የነፋስ ኃይል የማመንጨት እምቅ አቅም ቢኖራትም እስካሁን ማመንጨት የተቻለው 320 ሜጋ ዋት ብቻ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘ መረጃ ያመላክታል። የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 120 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ በምረቃው ወቅት መገለጹ ይታወሳል።