ቀጥታ፡

በፈጠራ ሥራቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተላቸው

አዲስ  አበባ   ጥቅምት  29/2012 በአገር ዓቀፍ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተላቸው። በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና በአጋር አካላት የተዘጋጀ አገር አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ ተወዳዳዎችን በመለየት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጠናቋል። በአውደ ርዕዩ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ በ200 ተማሪዎች፣ 11 መምህራንና በ10 የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ማዕከላት የተዘጋጁ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል። በዚህ የፈጠራ ውጤት እንደየክፍል ደረጃቸው ከአንድ እስከ ሦስት ደረጃ በመያዝያጠናቀቁ ተማሪዎች እያንዳንዳቸው የላፕቶፕና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በገንዘብ ሽልማቱ ከአንድ ሺህ እስከ ሦስት ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል። የተማሪዎችን የፈጠራ ውጤት ያበረታቱትና በመዝጊያ ፕሮግራሙ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እንደገለጹት፤ ያደጉት አገሮች ዛሬ የበለጸጉት በሳይንስ ላይ ትኩርት ሰጥተው በመስራታቸው ነው። ''ኢትዮጵያ እንድትበለግጽ ካስፈለገ ያለንን የተፈጥሮ እምቅ ኃይልና የሰው ሀብት በመጠቀም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ በስፋትና በትኩረት ሊሰራ ይገባል'' ብለዋል። የሳይንስ ምርምር ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸው፤ በተለይም ዘርፉን ለማሳደግ እየተዘጋጀ ባለው ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል። ''በተለይም ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድርስ በስርዓተ ትምህርቱ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያካትት ይደረጋል'' ብለዋል። ''መምህራንና ተማሪዎች ያሳዩት የፈጠራ ውጤት የሚያበረታታ በመሆኑ የመንግስት ድጋፍ ተናክሮ ይቀጥላል'' ያሉት ዶክተር ጥላዬ፤ የፈጠራ ውጤቱ ወደ ተግባር እንዲለወጥ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ዓለም አቀፉን የሳይንስ ቀን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ ለ4ኛ በዓለም ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ተከብራል። የፈጠራ ሥራቸውን በአውደ ርዕይው ያቀረቡት ተማሪዎች በበኩላቸው ልምድ የመለዋወጥ ዕድል የፈጠረ መድረክ እንዳገኙ ገልጸዋል። አቅም ለሌላቸው የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ከመንግስት እንዲደረግ ጠይቀዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም