በክልሉ ግጭቶችን ለማክሰምና የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የተደረገው እንቅስቃሴ ለውጥ አምጥቷል ... አቶ ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ግጭቶችን ለማክሰምና የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የተደረገው እንቅስቃሴ ለውጥ አምጥቷል ... አቶ ተመስገን ጥሩነህ
ባህር ዳር፤ ጥቅምት 30/ 2012 በአማራ ክልል የተከሰቱ ግጭቶችን ለማክሰምና የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የተደረገው እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በጉባኤው ላይ ባቀረቡት ሪፖርት በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ክልሉን ያጋጠሙት አደጋዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል። ከአዚህ ጋር ተያይዞ ሌላ ችግር እንዳይከሰት ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር በተሰራው ሥራ ችግሩ ባለበት እንዲቆም ያደረገ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል። ከግድያው ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የተጠረጠሩ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ መደረጉን ያስታወሱት አቶ ተመስገን፣ በቀጣይ የተደረሰበት ውጤት ለህዝቡ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል። በማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና አሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት የጸጥታ ኃይሉ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ለማስቆም መቻሉን ገልጸዋል። በተለይም የቅማንት የማንነት ጥያቄን የብሔር መልክ ለማስያዝ የተሞከረውን ጥረት እንዲከሽፍ መደረጉን ገልጸው፣ በረሃ ገብተው የነበሩ የኮሚቴ አባላትና ሌሎች አካላት በምህረት እንዲገቡ መደረጉ ትልቅ ስኬት መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህም ኑሯቸውን በገዳም ያደረጉ የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ "በቀጣይ ለእነዚህ ዓይነት አባቶች ክልሉ እውቅና በመስጠት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን ይሰራል" ብለዋል። በቀጣይም የክልሉ ምክር ቤት ቀደም ሲል በወሰነው ውሳኔ መሰረት የቅማንት የማንነት አስተዳደርን እውን በማድረግ የግጭቱን መንስኤ ለማክሰም ከሕብረተሰቡ ጋር ርብርብ እንደሚደረግ አመልክተዋል። ሰላምና ደህንነትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የክልሉን መደበኛ ፓሊስና ልዩ ኃይል በመገምገም የክልሉን ህዝብ መብትና ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የማስተካከል ሥራ መሰራቱ ለተገኘው ስኬት የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጉንም አቶ ተመስገን አመልክተዋል። "በክልሉ ሰዎችን አግተው ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል ያለአግባብ ሃብት የሚያካብቱ ህገ ወጦች አሉ" ያሉት አቶ ተመስገን፣ በነዚህ ኃይሎች ላይ የማያዳግም ርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል። ከአማራ ክልል ውጭ በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ መድረሱን ጠቁመው፣ ችግሩ እንዲቆም ለግጭቱ መንስኤ በሆኑ አካላት ላይ መንግስት ርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በሩብ ዓመቱ በተከናወኑ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አጭር ሪፖርት በማቅረብ ውይይት እየተደረገበት ነው። በአሁኑ ወቅት በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተደደር ዞን የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ እንዳይቀየርና በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የእህልና የእንስሳት መኖ የማቅረብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። እንደአቶ ተመስገን ገለጻ በምስራቅ አማራ በስምንት ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት ቢያደርስም ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመትና ጉዳቱ እንዳይባባስ ርብርብ እየተደረገ ነው። የምክር ቤት አባላትም በቅማንት የማነት ጥያቄ ሰበብ የግጭቱ ዋና ጠንሳሾችና አባባሾች የተሰጣቸውን የምህረት ዕድል ባለመጠቀማቸው አመራሩ ቆራጥ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል። ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ የክልሉን ሰባት የካቢኔ አባላት ሹመት ያጸደቀ ሲሆን የተለያዩ አዋጆችን ያጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።