ቀጥታ፡

ስራ አስፈጻሚው የመንግስት የልማት ተቋማት በከፊል ወደግል ይዞታ እንዲዛወሩ የያዙትን አቋም እንደሚደግፉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በአገሪቷ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የያዙትን አቋም እንደሚደግፉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። በተለይም የህዝቡን ፍላጎት ማርካት ተስኗቸው ለዘመናት የቅሬታ ምንጭ የነበሩት እንደ ኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ ኃይል በከፊል ወደግል ይዞታ እንዲዛወሩ በሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ምክንያት አሳማኝ መሆኑን ተናግረዋል። ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ምስራቅ ጌቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መሰረት ህዝብን ሲያማርሩ የነበሩትን  እንደ ኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ ኃይልን መንግስት በብቸኝነት መያዙ የዘርፉን እድገት ስለሚጎዳው ለውጡ ተገቢ ነው ብለዋል። ከጎረቤት ሀገራት ተሞክሮ ውጤታማነት ልምድ በመውሰድና የህዝቡን ፍላጎት በመረዳት ለጊዜው የሚመጥን አካሄድ ይዘው የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊደገፉ እንደሚገባም ተናግረዋል። በተለይም የህዝብ ብዛታቸው ከኢትዮዽያ በብዙ እጅ የሚያንሱ ጎረቤት ሀገራት በርከት ያሉ የግል የቴሌኮም ተቋማት እያላቸው የእኛ ሀገር መንግስት በብቸኝነት የያዘው ቴሌኮም ውድድር እንዳይኖር በማድረጉ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነቱ ደካማ እንዲሆን አድርጎታልም ብለዋል። በአገልግሎታቸው ደካማ ሆነው የቆዩት ኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የህዝብን ፍላጎት አርክተው በሚያገኙት ገቢ ሌሎች የልማት ስራዎችን መደገፍ ሲገባቸው በመንግስት ብቻ መያዛቸው የቅሬታ ምንጭ ሆነዋል ያሉት ደግሞ አቶ ብዙወርቅ መኮንን ናቸው። በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በዘርፉ የህዝብን ፍላጎት አርክተው በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ጭምር የሚሳተፉ አትራፊ ድርጅቶች ናቸው ያሉት አቶ ብዙወርቅ በኛ ሀገር ግን አሰራራቸው በተፈለገው መጠን እየሄደ አይደለም ብለዋል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት ወይዘሮ ስርጉት መላኩ በበኩላቸው መንግስት የበላይ ተቆጣጣሪነቱን ሳይለቅ ቴሌኮምንና ኤሌክትሪክ አገልግሎትን የመሳሰሉ ተቋማትን ወደ ግል  ዘርፍ ማስተላለፍ ለአገልግሎት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት ጠቃሚ ነው ይላሉ። የጠቅላይ ሚኒስተሩን ሁለገብ የለውጥ ሀሳቦች በመደገፍ ህብረተሰቡም ትብብር እንዲያደርግ ወይዘሮ ስርጉት ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ስራ አስፈጻሚው የወሰናቸውን ውሳኔዎች ተከትሎ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም