ቀጥታ፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎች አሳለፈ

ጥቅምት 29 / 2012  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 75ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ምክር ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በቅድሚያ የመከላከያ ሠራዊት መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሃሳብ አሳልፏል። መግለጫው እንዳስታወቀው በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አገራዊ ተልዕኮውን እንዲወጣና የለውጥ ማሻሻያ ስራዎችን ለማከናወን አዲስ አዋጅ ጸድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል፡፡ በአዲሱ አዋጅ ከተካተቱ አዳዲስ አደረጃጀትና መዋቅሮች ጋር ለማጣጣም፤ በስራ ላይ ባለው ደንብ የታዩ የአፈጻጸም ችግሮችን ለማስተካከል የመከላከያ ሰራዊት ደንብ ቁጥር 385/2008ን ማሻሻል አስፈልጓል። በተጨማሪም የመከላከያ ሰራዊቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል የሚረዱ አዳዲስ ድንጋጌዎች ለማካተት ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ ነበር ብሏል መግለጫው። የመከላከያ ሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸምና ሞራላዊ ዝግጁነት ለማጠናከር ሲባል ደንቡን መሻሻሉን የገለጸው መግለጫው የተሻሻለውን ረቂቅ ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎች በማከል ደንቡ በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።፡፡ በመቀጠልም ምክር ቤቱ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል። የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን በአሁኑ ወቅት በተግባር ስራዎችን እያከናወነ ያለበት ሁኔታ ላይ መሆኑን መግለጫው ገልጿል። ያም ሆኖ ከተጣለበት ኃላፊነት እና ዓላማውን ከመፈጸም አኳያ የደንቡ አንዳንድ ክፍሎች ግልጽነት ባለው መንገድ ያልተመላከቱ መሆኑን ተጠቅሷል። ስለሆነም የማቋቋሚ ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የመከላከያ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ደንቡ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የተመለከተው የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ስርዓትን ለመደንገግ በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ አዋጁ ሕገ መንግስቱ የተደነገገውን መንግስታዊ አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማናቸውም የመንግስት ባለስልጣን ሃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን የተመለከተ ነው። ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል። የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል። ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎች በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡ በመጨረሻም  ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መንግሥት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረገውን ስምምነት ለማጽደቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም