ቀጥታ፡

በሀገሪቷ ለሚከሰቱ ችግሮች ሀገራዊ መፍትሄ መስጠት ይገባል

ጥቅምት 29 / 2012 በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት መንስኤያቸውን በማጥናት የሚተነትንና ሀገራዊ መፍትሄ መስጠት የሚችል ተቋም መኖር እንዳለበት ተገለፀ። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሀገር በቀል እውቀቶች ጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ አብድልፈታሕ አብደላ እንዳሉት ግጭት ሀገርን፣ ህዝብንና መንግስትን ሁሉ የሚያከስር ነው። ማንም የማያተርፍባቸው ግጭቶች ሳይከሰቱ ለመከላከል ታዲያ ኀብረተሰቡን ማልማት የሚያስችሉ ቋሚ የህዝብ የመወያያ መድረኮች ሊኖር እንደሚገባም ተናግረዋል። የትምህርት፣ ፍትህና አስተዳደር ስርዓቱንም ሀገራዊ ማድረግ ሌላው መፍትሄ መሆኑን ገልፀዋል። አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፃፈው የመደመር መፅሀፍም ወደ ተግባር መቀየር ከተቻለ ጥሩ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችል መሆኑን እንደአብነት ጠቁመዋል አቶ አብድልፈታሕ። መንግስት በየአካበቢው ሰላምን ለማምጣትና ግጭቶችን ለመፍታት እየተሰሩ ያሉ የሀገር በቀል ስርዓቶችን ማጠናከርና መደገፍ እንዳለበትም ነው የመከሩት። እንደ ተቋምም ሀገሪቷን ሊያሻግሩ የሚችሉ ከ130 በላይ የህዝብ፣ የሀገርና መንግስት ስርዓት ላይ ጥናት መደረጉን ገልፀው፤  "መፍትሄ ካሻን እነዚህን ለዘመናት የዘለቁ ስርዓቶችን መጠቀም አለብን" ብለዋል። መንግስት እነዚህን ስርዓቶች 'ልጠቀም ብሎ የማይለው ስለምድን ነው? እስከመቼስ ለውስጣዊ ችግራችን የውጭ ሀገራትን ምክርና መፍትሄ እንጠቀማለን?' ሲሉም ይጠይቃሉ። ግጭቶች እንዲከሰቱ የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚለውን ማጥናትና በግጭቶች ዙሪያ ጥናትና ምርምር ማካሄድ ይገባልም ነው ያሉት አቶ አብድልፈታሕ። የግጭቶችን ደረጃን በማጥናት ይፋ የሚያደርግ ተቋም ከሌለ "ግጭቶችን አሳንሶ ወይም አጉልቶ ለማየትና ለመደናገር እንደሚዳርግም" ተናግረዋል። ግጭቶች ሲከሰቱ ብቻ ሳይሆን ሳይከሰቱም ጭምር ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ ጉዳዮችን በጥናት በመለየት የሚተነትን ተቋም ሊኖር እንደሚገባም ገልፀዋል። የኃይማኖት አባቶች መልአከ ገነት ዘውዱ ካሴ ና ሼህ ሀሚድ ሙሳ በበኩላቸው ግጭትን ለመከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው፤  በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣቱ ትልቁን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል። የኃይማኖት አባቶቹ ግጭት በየትኛውም ኃይማኖት የሚከለከል በመሆኑም "ማንኛውም አማኝ ለራሱ እንዳይሆን የማይፈልገውን በሰው ላይ እንዳይፈፅም" በፈጣሪ ስም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የእምነት ተቋማት  ስለሰላም እየሰበኩ እንዳሉ የገለፁት የኃይማኖት አባቶቹ፤ አሁንም ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ውለው ሳያድሩ እንዲፈቱና እርቀ ሰላም እንዲወርድ እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች አባቢያ አባ ጆቢር ከኢትዮጵያ ሽማግሌዎች የሰላም ህብረት ና ፕሮፌሰር ብርሃኑ መንግስቱ ከአሜሪካ የኢትዮጵያ የመግባባት ገንቢ መድረክ ናቸው። እስካሁን ግጭቶች ሲከሰቱ እርቅ ለማውረድ ካደረጉት ጥረት በተጨማሪም በቅርቡ በተከሰተው ግጭት ዙሪያም የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር መታሰቡን አስረድተዋል። በቅርቡም የኢትዮጵያ ሽማግሌዎች የሰላም ህብረት የሚል መዋቅር በመፍጠር በየአካባቢው ያሉ የሽምግልና ስርዓቶች ሀገራዊ ይዘት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን በማከል። መዋቅሩ መፈጠሩ ግጭቶች ከተፈጠሩ በኋላ ብቻ ሳይሆን ሳይፈጠሩም በፊት ህዝቡን የማወያየትና ማስተማሪያ መድረክ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። ግጭቶችን ለመከላከል መንግስት ህዝቡን ማድመጥ እንዳለበት ገልፀውም ህዝቡም መንግስት ሲሳሳት በተረጋጋ መልኩ ማረም እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ህዝቡ "እዚያ ማዶ የነደደ እሳት ወደ እርሱ መጥቶ ሳይፈጀው" በፊት ያገባኛል ብሎ መነሳት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። መንግስት ከመስመር የወጣን፤ በጎ ነገርን የማይሰማን ሰው መቆጣጠርና ለህግ ማቅረብ እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል። ግጭት ሰው ሰራሽ በመሆኑና ሁልጊዜም ቢሆን ተመሳሳይ ሃሳብና ፍላጎት በሌላቸው ሁለት ቡድኖች መካከል የሚከሰት በመሆኑ ለመፍትሔው ሶስተኛ መንገድ መፈለግ እንደሚገባም ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም