ፖሊስ የሚያደርገው ማሻሻያ ከአገሪቱ ለውጥ እኩል ለመራመድ የሚያስችለው መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ፖሊስ የሚያደርገው ማሻሻያ ከአገሪቱ ለውጥ እኩል ለመራመድ የሚያስችለው መሆኑን ገለጸ
ኢዜአ/ ጥቅምት 29 /2012 የፖሊስ ተቋማት የለውጥ ማሻሻያ ስራዎች ከአገሪቱ ለውጥ እኩል ለመራመድና አሰራርን ለማዘመን የሚያግዝ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ባሉ የፖሊስ ተቋማት የለውጥ ማሻሻያ ስራዎች እየተካሄዱ ነው። የማሻሻያው የትኩረት አቅጣጫዎች በሕግ አሰራርና መዋቅር ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን የማሻሻል፣ የሰው ኃይሉን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም የማሳደግ፣ ለፖሊስ ተልእኮ አስፈላጊ የሆኑ ቁሶችን የማሟላትና አስተዳደሩን የማሻሻልተግባር ናቸው። በተጨማሪም ፖሊሳዊ አገልግሎቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስደገፍና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት የማጠናከር ስራም እንዲሁ በለውጥ ማሻሻያው ተካትቷል። የማሻሻያው ዋና ዓላማ በተቋማቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ የሆነ እና የተሟላ ቁመና ያለው ባለሙያ ማፍራትና በተቋማቱ ላይ የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግሮችን በመሰረታዊነት መፍታት ነው። አቶ ጄይላን እንዳሉት የፖሊስ ተቋማቱ የአስፈላጊ ቁሶች አቅም አሁን ካለው ተልዕኮ ስፋትና ዘመኑ ያፈራቸውን ትጥቆች ከመያዝ አንፃር ያለባቸውን ክፍተት ማስተካከልንም ይጨምራል ማሻሻያው። በተቋማቱ የሚነሱ የመልካም አስትዳደር ችግሮችን በመፍታትም ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት አማራጭ የሌለው በመሆኑም ለውጡ ማስፈለጉን ነው አቶ ጄይላን የገለጹት። በዋናነት ትኩረት ያደረገው የሰብዓዊ መብት አያያዝና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል። የለውጥ ማሻሻያው አሰራሩን የሚያዘመንና ወቅቱ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር እንዲራመድ የሚያስችለውም ነው። የኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ የማሻሻያ ረቂቅ ተዘጋጅቶ እና በየደረጃው የሚገኙ አመራርና አባላት ተወያይተውበት ለሚመለከተው አካል መላኩንም አቶ ጄይላን አስታውቀዋል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአሜሪካ፣ ከጀርመን፣ ከቤልጂየም፣ ከህንድ ከሩዋንዳ እና ከሱዳን ልምድ በመቀመር የለውጥ ማሻሻያውን ማዘጋጀቱ ተነግሯል።