ቀጥታ፡

በትግራይ ደቡባዊ ዞን አንበጣን ከመከላከሉ በተጓዳኝ የደረሰ ሰብልን የመሰብሰቡ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ማይጨው ኢዜአ 29/2012፡- በአካባቢው የተከሰተው የአንበጣ መንጋን ከመከላከሉ በተጓዳኝ የደረሰ የሰብል ምርትን የመሰብሰብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ገለጸ። የመምሪያው  ተወካይ አቶ አሰፋ አስረስ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአንበጣ መንጋው አሁንም በአጎራባች ክልል  አድርጎ በራያ አላማጣና በኦፍላ ወረዳዎች ተከስቷል። አዝርዕትን ጨምሮ ሌሎች እፅዋት የሚያወድምው የበረሃ አንበጣ ለተወሰኑ ወራት ሊቆይ ስለምችል ጉዳት ከማድረሱ በፊት የደረሱ ሰብሎች የመሰብሰብ ስራ ትኩረት ተሰጥቷል። የገብስ ሰብል ሙሉ በሙሉ መሰብሰቡን ያመለከቱት አቶ አሰፋ "የስንዴ እና ጤፍ ሰብል ደግሞ 60 በመቶ የሚሆነውን ለመሰብሰብ ተችሏል" ብለዋል። አርሶ አደሩ የአንበጣ መንጋን ከመከላከሉ በተጓዳኝ የደረሰ ሰብልን በተቀናጀ መልኩ የመሰብሰቡ ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። የራያ አዘቦ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ ግርማይ በበኩላቸው በወረዳው ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ለጊዜው መቆጣጠር ቢቻልም አሁንም ሌላ ስጋት በመኖሩ አርሶ አደሩ የደረሰ ሰብልን  በፍጥነት እንዲሰበስብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። በወረዳው አብዛኛውን የጤፍ ምርት መሰብሰቡን ጠቁመው  የማሽላ  ሰብል ግን ባለመድረሱ መከላከል ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የአንበጣ መንጋ  በወረዳው ሊከሰት እንደሚችል አሁንም ስጋት ስላለ ከባለሙያዎችና ከአርሶ አደሮች የተውጣጣ ግብረ ኃይል እስከ ቀበሌ ድረስ ተደራጅቶ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ በራያ አላማጣና በኦፋላ ለሶስተኛ ጊዜ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከብዛቱና ከሸፈነው መሬት ጋር ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው የገለጹት ደግሞ የራያ አላማጣ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋአለም ተስፋስለሴ ናቸው፡፡ "ህብረተሰቡ ተስፋ ባለመቆረጥ  የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል  እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያበረታታ ነው "ብለዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት የአንበጣ መንጋው አሁን ያረፈበት ቦታ በብዛት የንብ ማነቢያ ስፍራዎች  ኬሚካል ለመርጨት አስቸጋሪ በመሆኑ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው። አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ ከመከላከል ጎን ለጎን  የደረሰ ሰብልን  የመሰብሰብ ስራ እያከናወነ ይገኛል። በ2011/2012 የምርት ዘመን በደቡባዊ  ዞን   በሰብል ዘር ከተሸፈነው ከ144 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መሬት አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የግብርናና ገጠር ልማት መምሪያው አመልክቷል፡፡ በክረምቱ ከዝናብ መዘግየትና መቆራረጥ ጋር የአንበጣ መንጋ ጉዳት ተጨምሮበት የምርት መቀነስ እንደሚያስከትል ተጠቁሟል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም