ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓል ሲያከብር የአገሪቷን ሰላምና አንድነት በማጠናከር ሊሆን ይገባል--ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓል ሲያከብር የአገሪቷን ሰላምና አንድነት በማጠናከር ሊሆን ይገባል--ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ
ኢዜአ ጥቅምት 29/2012 ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድን በዓል ሲያከብር የአገሪቷን ሰላምና አንድነት የሚያጠናክርበትና የነቢዩ መሐመድ አስተምህሮቶችን የሚተገብርበት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ገለፁ። መውሊድ በእስልምና የዘመን አቆጣጠር ዘመነ ሂጅራ ራቢአል አወል የተሰኘው ሶስተኛው ወር በገባ በ12ኛ ቀን በየዓመቱ ይከበራል። የቃሉ ምንጭ አረብኛ ሲሆን ትርጉሙም የመወለጃ ቦታ ወይም እለት ማለት ነው። መውሊድ በመንፈሳዊ ትርጉሙ ነብዩ መሐመድና የሱፊ ሼኺዎች የተወለዱበትን ወይም የሞቱበትን ዕለት ለማሰብ የተሰጠ ስያሜ ነው። የነብዩ መሐመድ የልደት ቀንም "መውሊድ አንንቢ" ተብሎ በመጠራት በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ የእምነት ስርዓት በድምቀት ተከብሮ ይውላል። ዛሬም 1 ሺህ 494ኛው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በመላ አገሪቷ እንዲሁም በታላቁ አንዋር መስጊድ እየተከበረ ይገኛል። በበዓሉ አከባበር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ፤ ነብዩ መሐመድ በምድር ላይ ሳሉ ሰላም ፍቅርና አንድነትን በማስተማር አርዓያ የነበሩ ነብይ ነበሩ ብለዋል። ነብዩ መሐመድ ይህ መልካም ፀባያቸው በመላው ዓለም እንዲወደዱ ስላደረጋቸውም ስማቸው እየነገሰ በየዓመቱ የልደት በዓላቸው ይከበራል ብለዋል። ህዝበ ሙስሊሙም የነብዩ መሐመድን መልካም ጸባያቸውንና አስተምህሮቶችን በመውሰድ የአገሪቷን ሰላምና የህዝቦቿን አንድነት ለማጠናከር መስራት እንደሚገባው ተናግረዋል። ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በመተሳሰብ፣ የተቸገሩ ወገኖቹን በመርዳትና የአገሪቷን ሰላምና አንድነት ለማምጣት በመፀለይ ሊሆን እንደሚገባም በማሳሰብ። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ሼኽ መሐመድ ሽፋ በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ ለአገሪቷ ሰላምና አንድነት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል። በቅርቡ በአገሪቷ በደረሰው ችግር ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ መሰል ችግር ዳግም እንዳይከሰት ህዝበ ሙስሊሙ በአንድነት በመሆን ሊያወግዝና ሊከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል። 1 ሺህ 494ኛው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) ዛሬ በመላ ሀገሪቷ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሥነ ስርዓቶች ነው እየተከበረ የሚገኘው።