አቶ አሊ ከድር የስልጤ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ - ኢዜአ አማርኛ
አቶ አሊ ከድር የስልጤ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ

ጥቅምት 28/2012 የስልጤ ዞን ምክር ቤት አቶ አሊ ከድርን የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ። ምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 5ኛ አስቸኳይ ጉባኤዉን ዛሬ በወራቤ ከተማ አካሂዷል፡፡ በጉባኤው ላይም ወደ ክልሉ እንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊነት የተሾሙትን የቀድሞውን ዋና አስተዳዳሪ ዘይኔ ቢልካን በመተካት ዞኑን እንዲመሩ በምክትል ዋና አስተዳዳሪነት የአቶ አሊ ከድርን ሹመት አጽድቋል። አቶ አሊ ቀደም ሲል ከወረዳ ጀምሮ እስከ ዞን አመራርነት በነበራቸው ቆይታ አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡና በዞኑ እየተካሔደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴም ያስቀጥላሉ ተብሎ የሚታመንባቸው መሆናቸውም ተገልጿል። አዲስ የተሾሙት የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ በበኩላቸዉ በዞኑ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከግብ ለማድረስ የተሰጣቸዉን ኃለፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ በመግለጽ የዞኑ ህዝብም ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል። ተሿሚውም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ-መሃላ በመፈጸም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተረክበዋል።