ጂዊሽ ቮይስ ኢንተርናሽናል የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የነፃ የህክምና አገልግሎት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ጂዊሽ ቮይስ ኢንተርናሽናል የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የነፃ የህክምና አገልግሎት ሰጠ
ጥቅምት 28/2012 ጂዊሽ ቮይስ ኢንተርናሽናል የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ባለፉት አምስት ቀናት በአዲስ አበባ በአንድ ጤና ጣቢያ ከ8 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የነፃ ህክምና አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ። ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከእሁድ ጥቅምት 23 እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሰጠው ነፃ የዓይንና የጥርስ ህክምና ለ8 ሺህ 837 ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አድርጓል። የነፃ ህክምና አገልግሎቱን የሰጠው በአዲስ አበባ በተለምዶ ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ህዳሴ ጤና ጣቢያ መሆኑ ታውቋል። በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር አዳነ በራሳ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ህክምናውን ካገኙት መካከል 108ቱ ሰዎች የዓይን ሞራ እና የግላኮማ ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸዋል። ለ3 ሺህ ሰዎች ደግሞ ነፃ የዓይን መነጽር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቁመዋል። በነፃ የህክምና አገልግሎቱ አቅመ ደካሞች፣ ገንዘብ ከፍለው መታከም የማይችሉ እና ቤት ውስጥ የዋሉ አረጋዊያን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል። የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ያለባቸው ህሙማን የህክምናው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጋቸውንም ዶክተር አዳነ ተናግረዋል። እንደ ዶክተር አዳነ ገለጻ በጥርስ ህክምና 1 ሺህ 988 ሰዎች የነፃ ህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በተሰጠው ነፃ የዓይንና የጥርስ ህክምና አገልግሎት 4 ሺህ 557 ወንዶችና 4 ሺህ 280 ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። የበጎ አድራጎት ደርጅቱ ከሚሰጠው ነፃ የህክምና አገልግሎት በተጓዳኝ ለጤና ባለሙያዎች የእውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የማድረግ ዕቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል። ድርጅቱ ላለፉት 20 ዓመታት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን እስካሁንም ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የነፃ ህክምና አገልግሎት ሰጥቷል።