ቀጥታ፡

የደደቢት ስፖርት ክለብ ከኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ራሱን አገለለ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 የደደቢት ስፖርት ክለብ ከ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ። ደደቢት ነገ በጅማ ስታዲየም ከጅማ አባጅፋር ጋር የጥሎ ማለፍ ጨዋታውን እንዲያደርግ መርሃ ግብር ወጥቶለት ነበር። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደ መስቀል ለኢዜአ እንደገለጹት ከወጪና ከጸጥታ ጉዳይ አንጻር ደደቢት በጥሎ ማለፍ ውድድሩ ላይ አይሳተፍም። ክለቡ ነገ ከጅማ አባጅፋር ጋር በጥሎ ማለፉ ተጫውቶ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከአርባምንጭ ጋር ጨዋታውን አድርጎ በተወሰኑ ቀናት ልዩነት አሁንም ከጅማ አባጅፋር ጋር ለመጫወት ወደ ክልል መውጣቱ ክለቡን ከልክ በላይ የሆነ ወጪ የሚያስወጣው በመሆኑ ራሱን ከውድድሩ አግልሏል ብለዋል። በተጨማሪም በክልል ከተሞች ያለው ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳይ፣ በክልል ስታዲየሞች የሚታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለትና በክልል በሚደረጉ ጨዋታዎች ያለው የዳኝነት ውሳኔ ፍትሓዊ አለመሆኑ ክለቡ ከጥሎ ማለፉ ራሱን እንዲያገል ያደረገው ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል። ውሳኔው የተወሰነው የደደቢት ስፖርት ክለብ አመራር ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ መሆኑንና ክለቡ ከውድድሩ ራሱን ቢያገል አዋጪነትና ተገቢነት ያለው ነው የሚል አቋም መያዙን ተናግረዋል። ክለቡ ራሱን ከኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ውድድር ራሱን ቢያገልም ደደቢት ቀሪ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መርሃ ግብር ላይ እንደሚጫወት ነው አቶ ሚካኤል ያስረዱት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ፤  ክለቡ ከውድድሩ ራሱን ማግለሉን ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጸው የደደቢት ጥያቄ አግባብነት አለው የለውም የሚለውን ጉዳይ የሊግ ኮሚቴው ተመልክቶ ዛሬ በሚያደርገው ስብስባ ውሳኔውን ያሳውቃል ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም