ቀጥታ፡

የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሜ ከ80 በመቶ በላይ ነው አለ

የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በገቢ አሰባሰብ፣ ፊዚካልና መደበኛ ሥራውን ፋይናንስ በማድረግና በክትትልና ድጋፍ ዕቅድ አፈጻጸሙ ከ80 በመቶ በላይ ማስመዝገቡን ገለጸ። ለአፈጻጸሙ ስኬት ጽህፈት ቤቱ ባለፉት ሶስት ወራት ዕቅዱን መነሻ ያደረጉ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር  በማከናወኑ መሆኑን አስታውቋል። በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ገቢ አሰባሰብ ከ665 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ አፈጻጸሙን 81 ነጥብ 07 በመቶ ማድረሱን ገልጿል። ከነዳጅ ታሪፍ 649 ሚሊዮን፣ ከተሸከርካሪ ዘይትና ቅባት 1 ሚሊዮን፣ ከመንገድ ጠቀሜታ ክፍያ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እና ከግምጃ ቤት ሠነድ ግዢ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር  ገቢም ሰብስቧል። ክብደት ላይ መሰረት ባደረገ ዓመታዊ የተሸከርካሪ ፈቃድ ዕድሳትም 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና የክልል የመንገድ ኤጄንሲዎችን በማሳተፍ በሩብ ዓመቱ በወቅታዊ ጥገና 1 ሺህ 479 ኪሎ ሜትር መንገድ የተጠገነ ሲሆን የ106 ኪሎ ሜትር መንገድ መደበኛ ጥገናም አከናውኗል። በዚህም የፊዚካል አፈጻጸሙን 94 በመቶ ማድረሱን ነው ጽህፈት ቤቱ ያስታወቀው። በመንገድ ፈንድ በጀት ሥራዎችን ፋይናንስ ከማድረግ አኳያ በሩብ ዓመቱ  70 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለገጠር መንገድ ኤጀንሲዎች ቅድመ ክፍያ ብቻ ፈጽሜያለሁም ነው ያለው። በገቢ አሰባሰብ፣ በክፍያ አፈጻጸም፣ በመንገድ ጥገናና ደህንነት የጥራት ደረጃ ለማስጠበቅ ባደረገው ክትትልና ድጋፍ ክፍተት ያለባቸው ተግባራትና አሰራሮችን በማጥናት ወጥ የአሰራር ስርዓትና ግልጽነት እንዲኖር ማድረጉን ገልጿል። በሌላ በኩል በክብደት ላይ ከተመሰረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ዕድሳት ገቢ በተሰበሰበው መጠን ወደ ፈንዱ አካውንት አለመግባቱን እንደ ተግዳሮት አንስቷል። ገንዘቡን ወደ ፈንዱ አካውንት ለማስገባት ክትትሉን አጠናክሮ በማስቀጠልና ጥናት በማድረግ ገቢው ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ችግሮችን መፍታቱንም ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም