ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ማሾ ግብይት እየጨመረ ነው

ጥቅምት 28/2012 በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ማሾ ግብይት እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ። የአረንጓዴ ማሾ ግብይት በምርት ገበያ ብቻ እንዲከናወን በተወሰነው መሰረት ካለፉት ወራት በበለጠ በጥቅምት ወር ግብይቱ ጨምሯል። በዚህም 6 ሺህ 46 ቶን ምርት በ168 ሚሊየን ብር መገበያየት መቻሉን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ይህም ካለፈው መስከረም ወር ጋር ሲነፃፀር የግብይት መጠኑ በ19 በመቶ፤ በዋጋ ደግሞ በ7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል። በተመሳሳይ እንደ አረንጓዴ ማሾ ግብይቱ የቀይ ቦሎቄ ግብይትም በወሩ 190 ኩንታል ቀርቦ በ184 ሺህ ብር ተገበያይቷል። ቀጣዮቹ ወራት የምርት ጊዜ በመሆኑ በስፋትይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ይታመናል። ከዚህ በተጨማሪም ምርት ገበያው በጥቅምት ወር 21 ሺ 34 ቶን ቡና፣ 9 ሺህ 434 ቶን ሰሊጥ፣ 6 ሺህ 534 ቶን አኩሪ አተርና 1ሺህ 327 ቶን ነጭ ድቡልቡል ቦሎቄ እንዳገበያየ ገልጿል። ከእነዚህ መካከልም ቡና የግብይት መጠኑን 47 በመቶ፣ የግብይት ዋጋውን ደግሞ 67 በመቶ በመያዝ ቀዳሚ ነው። ከዚህ ውስጥ 13 ሺህ 947 ቶን ያልታጠበ ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ938 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር እንዲሁም 10 ቶን የታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ588 ነጥብ 1 ሺህ ብር ተገበያይቷል። ለአገር ውስጥ የሚቀርብ 6 ሺህ 309 ቶን ቡና በ432 ነጥብ 78 ሚሊየን ብር፣ 767 ቶን ስፔሻሊቲ ቡና ደግሞ በ71 ነጥብ 14 ሚሊየን ብር ግብይቱ መከናወኑም ተጠቁሟል። በሌላ በኩል የሰሊጥ ግብይት ካለፈው ወር ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠንና በዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን የግብይት መጠኑም በ136 በመቶ እንዲሁም የግብይት ዋጋው በ88 በመቶ ጨምሯል ተብሏል። በዚህ ወር 9 ሺህ 434 ቶን ሰሊጥ በ419 ነጥብ 75 ሚሊየን ብር ሲሸጥ ሁመራ/ጎንደር በግብይት መጠንና ዋጋ 61 እና 66 በመቶ በመያዝ አንደኛ ደረጃ ይዟል። ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የሰሊጥ ግብይት በመጠን የ26 በመቶ፤ እንዲሁም በዋጋ የ32 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ነው የተገለጸው። ግብይቱ እየተጠናከረ የመጣው አኩሪ አተርም በወሩ 6 ሺህ 534 ቶን በ105 ነጥብ 88 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል። በተጨማሪም 1 ሺህ 346 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ28 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የተገበያየ ሲሆን ይህም ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በግብይት መጠን 57 በመቶ፣ በግብይት ዋጋ ደግሞ 39 በመቶ ከፍ ማለቱ ተገልጿል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጥቅምት ወር ብቻ 44 ሺ 394 ቶን ምርት በ2 ነጥብ 16 ቢሊየን ብር ማገበያየቱን በመረጃው አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም