ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ግብጽ የህዳሴው ግድብን አስመልክቶ በአሜሪካ ምክክር አድርገዋል

አዲስ አበባ ጥቅምት  28/2012 በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ የምክክር ስብሰባ ላይ ተሳትፎ ተመልሷል:: ኢትዮጵያ በስብሰባው የተሳተፈችው በአሜሪካ መንግስት ጋባዥነት ሲሆን ጥሪው በግድቡ ላይ የሚደረግ ምክክር እና ሂደቱን ለማስቀጠል አልሞ የተዘጋጀ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜ ያደረሰው መግለጫ ያሳያል። በዚሁ አጋጣሚ የአሜሪካ መንግስት በግድቡ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ላሳየው አጋርነት የኢትዮጵያ መንግስት ምስጋና አቅርቧል። ምክክሩ በዋይት ሃውስ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲሁም ከአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቴቨን መኒቺን እና የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ በተገኙበት ደግሞ በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር የተደረገ ነው። ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ፍትሃዊና ሚዛናዊ የውሃ መብት እንዳላትም አስገንዝባለች። ኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኝ ህዝቧን ተደራሽ ለማድረግ እና ለድህነት ቅነሳ ጥረቷ እንጂ ማንንም አካል የመጉዳት ዓላማ እንደሌላት ማስረዳቷ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ለሶስትዮሽ ውይይቱ አሁንም ትልቅ ግምት እንደምትሰጥ በመግለጽ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ማናቸውም አለመግባባቶች በቴክኒክ ባለሙያዎች ሙያዊ ምክክር ብቻ እንደሚፈቱም እንደምታምን አስታውቃለች። ጉዳዩን ኢ-ምክንያታዊ ያልሆነ የፖለቲካ ይዘት ማላበስም ለአገራቱ እንደማይጠቅም አስገንዝባለች። ይህም በተሳታፊዎቹ ዘንድ የነበረውን ብዥታ ግልጽ እንዲሆንና የኢትዮጵያ አቋም ገንቢ መሆኑን እንዲገነዘቡ አስችሏል። በተጨማሪም የቴክኒክ ውይይቱ እንዲቀጥል እንዲሁም ለቴክኒክ ኮሚቴው ድጋፍ ለማድረግ እና በሚኒስትሮች ደረጃ ያለው ውይይት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2015ቱ የመርሆዎች ስምምነት መሰረት እንዲቀጥልም ከመግባባት ላይ ተደርሷል። አሜሪካ እና የዓለም ባንክ የቴክኒክ ውይይቱ እንዲቀጥል ማበረታታቸውንና በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶችም በታዛቢነት እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ምናልባት በቀጣይ የሚደረጉ ውይይቶች ለመጨረሻ ውሳኔ ባያደርሱ፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2015 በተፈረመው የመርሆዎች ስምምነት ሶስቱም አገራት በሚያደርጉት ውሳኔ ሊመረጥ እንደሚችልም መግባባት ላይ ተደርሷል። የግብጽና የኢትዮጵያ መሪዎች በቅርቡ በሩሲያ ተካሂደ በነበረው የሩስያ-አፍሪካ ጉባኤ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት በሰጡት መመሪያ መሰረት የሶስቱ አገራት ብሔራዊ የቴክኒክ ቡድን ገንቢ ወደ ሆነ ምክክር እንዲመለስ ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች ተብሏል። ለዚህም የሶስቱን አገራት ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ ለስብሰባ ጠርታለች። በመጨረሻም ኢትዮጵያ ውይይቱ በዚሁ የትብብር መንፈስ እንደሚቀጥል እንደምታምንና ሁሉም አሸናፊ ሊሆን በሚችልበት መድረክ ላይ ትኩረት እንዲደርግ ኢትዮጵያ ጥሪዋን ታቀርባለች ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም