ቀጥታ፡

የግብርናው ዘርፍ ከኋልዮሽ ጉዞ እንዲወጣ አፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል-ጥናት

ጥቅምት 28/2012 የኢትዮጵያ ግብርና ዘመናዊ አሰራርን ባለመከተሉና በባህላዊ መንገድ በመከናወኑ እንደካሮት ቁልቁል እያደገ መጥቶ የምግብ ዋስትና ያላረጋገጠች አገር እንድትሆን አድርጓታል ሲል ጥናት አመለከተ። በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት "ሐገር በቀል እይታ ለኢትዮጵያ ግብርና" በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመክሯል። የመወያያ ጥናቱን ያቀረበው ዶክተር ጸደቀ አባተ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያ ግብርና ከባህላዊ መንገድ ወጥቶ ዘመናዊ ስርዓትን ባለመከተሉ ካለው የረጅም ታሪክ አንጻር እስካሁን የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና እንዲያረጋግጥ መፍትሔም አልተበጀለትም ይላሉ። ኢትዮጵያ ካላት የረጅም ዘመን ግብርና ልምድና በዘርፉ በስፋት እንደመሰማራቷ መጠን "ለዓለም ገበያ ሊታቀርብ ቀርቶ በአስተማማኝ ሁኔታ የምግብ ዋስትናዋን እንኳ ማርጋገጥ አልቻለችም" ይላሉ። በመሆኑም ግብርናው አሁን ካለው  ኋላቀር የማምረት ዘዴ እንዲወጣና ዘመናዊ የግብርና ስርዓት ለመከተል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአፋጣኝ መፍትሔ ሊያበጁለት ይገባልም ብለዋል። በተለይም ደግሞ በአገሪቷ እየታየ ያለው ፈጣን የህዝብ እድገት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ መዋቅራዊ ተግዳሮቶች፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት፣ የእርሻ መሬት ጥበትና የአፈር መሸርሸር በቀጣይ ግብርናውን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከሚተቱት መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል ዶክተር ጸደቀ። በተጨማሪም የግብርናው ምርት የወጭ ንግድ እየቀነስ መሄድ፣ የሸመታ ዋጋ እየናረ መምጣት፣ በግብርናው ምርቶች ምንም እሴት ሳይጨመር ወደ ውጪ መላካቸው፣ ምርታማነት መቀነስና የአዝርዕት በሽታ እንዲሁ የዘርፉን ስኬት ከሚያከብዱት መሆናቸውን ዶክተሩ አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ  እ.አ.አ 2050 ደግሞ 190 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል። ስለሆነም የግብርናውን ዘርፍ በህዝቡ ቁጥር ልክ ማዘመንና ማሻሻል ካልተቻለ ኢትዮጵያን በምግብ ዋስትና ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚከታት ይገልጻሉ ዶክተር ጸደቀ። በተመሳሳይ በእንስሳት ግብርና ዘርፍም ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላትና ከፍተኛ ቁጥር የያዘች ቢሆንም የእንስሳት ተዋጽኦ አቅርቦትና ጥራቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱን ገልጸዋል። የሰብሎችን ስብጥር መጨመር፣ የሰብልን ጉዳትና ብክነት መቀነስ፣ አዳዲስ አካባቢዎችን ማልማት፣ እሴት መጨመር፣ የቴክሎሎጂ ስርጸትና የአግልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግና መስፋፋት ደግሞ ከወዲሁ ሊሰሩ የሚገቡ ስራዎች መሆኑን ጠቁመዋል ተመራማሪው። በተጨማሪም አስተዳደራዊ የሆኑ ጉዳዮችን ማስተባበርና የዓለም አቀፍ ሽርክናን መፈተሽ፣ በእጃችን ያሉትን ቴክኖሎጂዎችን ማደስ፣ ሐገር በቀል ሰብሎችን ስራ ላይ ማዋልና የዘመናዊ ሳይንስ ስርዓት መከተል እንዲሁም የመስኖ ልማት መጠቀምና ማስፋፋት ጊዜ ሊሰጣቸው የማይገቢ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል። በዚሁ ውይይት ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው አገሪቷ ካላት በርካታ የተማረ የሰው ኃይል አንጻር በግብርናው ዘርፍ ብዙ ምርምር እንዳልተደረገበት አልሸሸጉም። እንዲሁም የተማረ የሰው ኃይሉ ወደ ግብርናው ለመሰማራት ፍላጎት የሌለው በመሆኑ ዘርፉን ማሳደግና ውጤታማ ደረጃ ላይ ማድረስ እንዳልተቻለም ተናግረዋል። በተለይም ከሌሎች የውጭ አገሮች ተሞክሮዎችን በመቀመርና ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ግብርናውን ማዘመን እንደሚገባም ተናግረዋል። የ7 ሺህ ዓመታት ታሪክ እንዳለው የሚነገርለት የኢትዮጵያ ግበርና ማረሻን መጠቀም ከተጀመረ ከ500 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረም እንዲሁ መረጃዎች ያሳያሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም