ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን የስደተኞች ጊዜያዊ የመረጃና ማረፊያ ማዕከል ተቋቋመ

መተማ ሚያዝያ 29/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውሃ ከተማ ስደተኞችን በጊዜያዊነት ማቆየት የሚያስችል የስደተኞች መረጃና ማረፊያ ማዕከል ተቋቁሞ ለአገልገሎት ዝግጁ ሆነ፡፡ የዞኑ ማህበራዊ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ እንደተናገሩት መተማና አካባቢው ከሃገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሱዳን ለመሸጋገር እንደመውጫ በር ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህም በየዓመቱ ከ300 በላይ ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ለመውጣት ሲሞክሩ በመያዝ ወደ ትውልድ ቀያቸው ለመመለስ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመው ፤ "ከእይታ ውጭ ሆነው የሚሻገሩ ሰዎች ቁጥር በርካታ ነው "ብለዋል። ቀደም ሲል በህገ ወጥ ስደት አስወጋጅ ግብረ ሃይል አማካኝነት የሚያዙ ዜጎችን በጊዜያዊነት ማቆያ ማዕከል ባለመኖሩም ከፍተኛ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን የተቋቋመው ማዕከል ስራ መጀመርም ህገወጥ ተዘዋዋሪዎችን በመያዝና  መክሮ በማስተካከል ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። የፌደራል ፖሊስ ተወካይ ኮማንደር ደግነው አሰፋ በበኩላቸው በአካባቢው በየቀኑ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ለመሻገር የሚሞክሩ ህገ-ወጥ ስደተኞች እንደሚያዙ አመልክተዋል፡፡ በሀገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት የሚሞክሩትን ሰዎች  በአካባቢው ግብረ-ኃይል ቢያዙም ምቹ የማረፊያና መረጃ ማዕከል ባለመኖሩ በስራቸው ከፍተኛ ክፍተት ይፈጥር እንደነበር ተናግረዋል፡፡ "ይህ የመረጃና የማረፊያ ማዕከል መቋቋም ምቹ የስደተኞች አስተዳደር እንዲኖር ያደርጋልም "ብለዋል፡፡ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞች ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠንክረው እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ የመተማ ወረዳ ፍትህ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን መለሰ ናቸው፡፡ በዞኑ ፖሊስ መመሪያ የወንጀል ምርመራ የስራ ሂደት ባለቤት ዋና ኢንስፔክተር አሊ ገበየሁ በበኩላቸው ህገ-ወጥ ተዘዋዋሪዎች ከተያዙ በኋላ ማረፊያ ባለመኖሩና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አዳጋች ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች እስከ መተማ የመንቀሳቀስ መብት አለን ብለው ስለሚጠይቁ የመከላከል ስራውን አስቸጋሪና ውስብስብ እያደረገው ይገኛል፡፡ ስደተኞቹ ከሚመጡበት አካባቢ ግንዛቤው መፈጠርና የስደትን አስከፊነት ማሳወቅ እንደሚያስፈልግም ዋና ኢንስፔክተሩ አብራርተዋል። ማዕከሉ ጥምረት ለህይወት ኢትዮጵያ በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የተቋቋመ መሆኑን  በድርጅቱ የፕሮጀክቱ ማናጀር አቶ ሰሎሞን አበበ አመልክተዋል፡፡ አስከፊውን ህገ-ወጥ ስደት ለመከላከልና በተዘዋዋሪዎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ማህበራዊ ቀውሶችን ለመቀነስ የማረፊያና መረጃ ማዕከል ተቋቁሟል፡፡ በማዕከሉ የሴቶች፣ የህፃናትና የወንዶች ማረፊያ ክፍል እንዲሁም  የምክርና የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው " በተለይም በሴቶችና ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ ትኩረት አድርጎ ይሰራል"ብለዋል፡፡ የተቋቋመው ማዕከል  ጊዜያዊ ሲሆን በቀጣይ ቋሚ የስደተኞች ማረፊያና መረጃ ማዕከል የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት ለማስገንባት ከከተማ አስተዳደር ጋር ስምምነት ላይ መደረሱም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም