ታራሚዎችን ማረምና ማነጽ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ታራሚዎችን ማረምና ማነጽ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 28 ቀን 2012 ታራሚዎችን ማረምና ማነጽ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስታወቀ።
ማረሚያ ቤቶች የመብት ጥሰት የሚፈፀምባቸው፣መሰረታዊ ፍላጎት የማይሟላባቸው፣ለማረምና ለማነጽ አመቺ አይደሉም መባሉ ዜጎች በተቋሙ ላይ አመኔታ እንዲያጡ ምክንያት መሆኑን ሲገለጽ ይደመጣል።
ይህን ሁኔታ ለመቀየር የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የቀድሞውን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ በአዲስ መልክ ለማሻሻል የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አዋጅ በሚል ረቂቅ አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ላይ ነው።
ኢዜአ የተሻሻለው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከቀድሞ የህግ ማዕቀፍ ምን የተለየ አዲስ ነገር ይዞ እንደመጣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባስን አነጋግሯል።
ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ፣ አዲሱ አዋጅ በለውጥ መንፈስ የተቃኘ አገራዊ የለውጥ ስራ አካል ተደርጎ መወሰድ ይገባዋል ይላሉ።
ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቶች ለሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ክፍተቶች ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ያሉ ቢሆንም በዋናነት ግን የህግ ክፍተቶች መኖራቸውን አስረድተዋል።
ይህንን ክፍተት ለማስተካከል ቀድሞ የነበረው አዋጅ አገሪቱ አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሊሄድ በሚችል አዋጅ ተስተካክሎ መዘጋጀት ያለበት በመሆኑ ስራው መሰራቱን ተናግረዋል።
በአዲሱ አዋጅ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ አንድ ፖሊስና አንድ አመራር መወሰን የሚችለውንና የማይችለውን ተግባር የሚገድብ የህግ ማዕቀፍ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የታራሚዎችን መብትና ግዴታ በዝርዝር የሚያስቀምጥ አዋጅ መሆኑን ተናግረው በመሆኑም አዲሱ አዋጅ ፀድቆ ሲወጣ ለስራቸው ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
የማረሚያ ቤት ተልዕኮ ማረም እና ማነጽ ነው ያሉት አቶ ጀማል ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ይህን ተልዕኮ ለማስፈፀም ከህግ ማዕቀፍ ጀምሮ ክፍተት የነበረ በመሆኑ ታራሚዎችን አስሮ በማስቀመጥ ዝንባሌ ላይ ያተኮረ አዋጅና አሰራር እንደነበር አውስተዋል።
አዲሱ የህግ ማዕቀፍ እነዚህን አሉታዊ ሁኔታዎች በመቀየር ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን ማረምና ማነጽ በሚያስችላቸው መልኩ ተደራጅተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ታራሚዎች መማር፣ መሰልጠን የልማት ኃይል ሆነው መሰማራት አለባቸው ያሉት አቶ ጀማል ለዚህ ደግሞ በአዲሱ አዋጅ እነዚህን መብቶች ድጋፍ የሚሰጡ ህጎች መካተታቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ባለው የማረሚያ ቤቶች ገጽታም ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት በተሰራው ስራ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በፍትህ መጓደል በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የነበሩ ችግሮች መፈታታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የህግ ክፍተቶችን በመዝጋት፣ የተዘጋጁ አዋጆች፣መመሪያዎችና ደንቦች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንዲፀድቁ በማድረግ ለፈፃሚው አካል ደግሞ ግንዛቤ በማስጨበጥ የማረምና ማነጽ ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።