ቀጥታ፡

ለህዳሴ ግድብ በ1ኛ ሩብ አመት ከ168 ሚሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰብ ተሳትፎ ተሰብስቧል

ኢዜአ ጥቅምት 28/2012 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ አመት በህብረተሰብ ተሳትፎ 168 ሚሊዮን 953 ሺህ ብር ገቢ መገኘቱን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ጽህፈት ቤቱ ዛሬ በግድቡ ዙሪያ ያለውን የህብረተሰብ ተሳትፎ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብራሃም እንደገለጹት፤ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝና የህብረተሰቡ ተሳትፎም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የግድቡ ጉዳይ አገራዊ ብቻ ሳይሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መነጋገሪያ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል። በተለይም ከወቅቱ የግብፅ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሁሉም የአገሪቷ አቅጣጫዎች የሚገኙ ህዝቦች ተሳትፎ ዳግም በማንሰራራት ላይ እነደሚገኝና ድጋፋቸውን አጠናክረው እየቀጠሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ በህብረተሰብ ተሳትፎ በቦንድ ግዢ 168 ሚሊዮን 953 ሺ ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል። የህብረተሰቡ ተሳትፎ በዚሁ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነም በወር እስከ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የሚያስችል ሁኔታ መሆኑንም ገልጸዋል። በመሆኑም አገሪቷ በራሷ ህዝቦች ከአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን ግድብ ለመገንባት የወጠነችውን አላማ ለማሳካትም የውስጥ አንድነትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል። ለግድቡ በ2011 ዓ.ም በአጠቃላይ 970 ሚሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቦ እንደነበርም አውስተዋል አቶ ኃይሉ። የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን በአጠቃላይ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ 13 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡም ተገልጿል። እስካሁንም  6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚሆን ቦንድ ለግለሰቦች መመለሱም ተጠቁሟል። የግድቡ ግንባታም አሁን ላይ 69 በመቶ ደረጃ ላይ መድረሱን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም