በድምጽ ብክለት መቸገራቸውን የመቐሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በድምጽ ብክለት መቸገራቸውን የመቐሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
መቐሌ ጥቅምት 28 / 2012 በመቐለ ከተማ ማስታወቂያ በሚያስነግሩ ሰዎችና ድርጅቶች ከመጠን በላይ በሚለቀቅ ድምጽ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ታምራት የማነ እንዳሉት በከተማው በተሽከርካሪዎች እየዞሩ የተለያዩ ማስታወቂያዎች የሚያስነግሩ ድርጅቶች በድምጽ ማጉያ ከልክ በላይ በሚለቁት ድምጽ ሕብረተሰቡን እያወከ ነው። የድምጽ ማጉያ መጠናቸው ያልተገደቡ መሳሪያዎችን በመኪና ላይ በመጫን እንዲሁም በየተቋማቱና በመንገድ ዳር ተክለው ማስታወቂያ በሚያስነግሩ አካላት የድምጽ ብክለቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ስለሺ ሄኖክ ናቸው። "ማስታወቂያ አስነጋሪዎች ድምጽ ከፍ ብሎ የሚነገርበትና የማይነገርበት ቦታን አይመርጡም" ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል። መምህር ተስፋሁነኝ ኃይለማሪያም የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው እንዳሉት በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ በመኪና እየዞሩ የተለያዩ ሙዚቃዎችን በመጠቀም የንግድ ሸቀጦችን ለመሸጥና ለማስተዋወቅ ሚለቀቀው ድምጽ በተለይ በዕድሜ የገፉ ሰዎችንና ሕሙማንን እያወከ ነው። በገበያ ስፍራና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የሚለቀቀው የድምፅ መጠን በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ሰዎችን ስለሚረብሽ በገበያ ተረጋግቶ ለመሸመት እንቅፋት መሆኑን አመልክተዋል። "የሕክምና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የሚበዙባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ከመጠን ያለፈ ድምጽ እየተለቀቀባቸው እየታወኩ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ መድሃንዬ ክንፈ የተባሉ ነዋሪ ናቸው። አቶ ኪደነ ምህረተአብ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በከተማው ቀበሌ 16 እና ዓዲሓውሲ በተባሉ አካባቢዎች ከጭፈራ ቤቶችና ከመጠጥ ቤቶች ሳይመጠን የሚለቀቀው ድምጽ በመንገድ የሚያለፈውን ጭምር እያወከ መሆኑን አስረድተዋል። በከተማው አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ጀማል ካሕሳይ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የህብረተሰቡ ቅሬታ አግባብ መሆኑን ተናግረዋል። በከተማው በቀን እና በማታ የሚለቀቀው ድምጽ ከመጠን በላይ ያለፈና የከተማዋን ነዋሪዎች እያወከ መሆኑን አመልክተዋል። ህብረተሰቡ ለማስተማርም ሆነ በአጥፊዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድርግ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በጽህፈት ቤቱ ያለው የሰው ኃይል አንድ ሰው ብቻ በመሆኑ መቸገራቸውን አስረድተዋል።