ቀጥታ፡

መውሊድ “የአላመውሊድ “የአላህ” ምህረት የሚከጀልበት ታላቅ በዓል በመሆኑ ሁሉም በመከባበር እንዲያሳልፈው ጥሪ ቀረበ

ጥቅምት 28/2012 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በመጪው ቅዳሜ የሚከበረውን 1 ሺህ 494 ኛውን የመውሊድ በዓል አስመልክቶ ለመላው ሙስሊሞች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ በዓሉን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የሙስሊሙችን አንድነት ለማጠናከር የጀመርነው እንቅስቃሴ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል። ሆኖም ምክር ቤቱ በሁሉም አካባቢ መጅሊሶችን እያዋቀረ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች የመጅሊስ ምክር ቤቶችና መስጅዶችን መንጠቅ እየተስተዋለ መሆኑ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል። በከተሞች ኢማሞችንና ሙአዚኖችን፤ በገጠር መሻኢኮችንና ሙደሪሶችን የማስከፋትና ከስራ የማፈናቀል ድርጊት መኖሩንም ገልጸዋል። በሙስሊሙ ውስጥ “ሰለፍያ” እና “ሱፊያ” በማለት የመከፋፈል እሳቤዎች ነበሩ ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር አሁን ላይ በአንድነ ጉዳይ በእኩልነት እንዲመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም በተወሰኑ ክልሎች የአመራር ምርጫ የተደረገው ከአንድ ወገን ብቻ በመሆኑ ከሁለቱም በኩል በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል። በሃረሪ ፣ሶማሌ እና ድሬዳዋ ያሉትን የመጅሊስ አመራሮች የማስተካከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። "የአላህ መልእክተኛ ነብዩ ሙሃመድ" አንድነትን ያስተማሩ፣ ህዝባቸውን በወንድማማችነት ያስተሳሰሩ፣ ጥላቻን አውግዘው ፍቅርንና ሰላምን አብዝተው የሰበኩ መሆናቸው አብሮነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። መውሊድ ተራርቀው የሚኖሩ መሻኢኮች የሚገናኙበት፣ ደረሶችና ምስኪኖች ሶደቃ የሚቃመሱበት፣ ህዝበ ሙስሊሙ  ስለ እምነቱ ምክር የሚወስድበት፣ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር የሚተሳሰርበትና ለሀገር ሰላምና አንድነት ዱዓ የሚደረግበት፣ “የአላህ” ምህረት የሚከጀልበት ታላቅ በዓል መሆኑንም አውስቷል። አገራችንን ሰላም ያደርግልን ዘንድም “አላህን” በመለመን አንድነታችንን ማጠናከር ኢትዮጵያ ሁላችንም በፍቅር የምንኖርባት እንዲትሆን ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን በመመኘት ለመላ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም