ቀጥታ፡

የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ስራዎችን የሚደግፍ የፋይናንስና የማበረታቻ ስርዓት ያስፈልጋል - ጥናት

ጥቅምት 27 / 2012 በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ስራዎችን በበቂ ሁኔታ የሚደግፍ የፋይናንስና የማበረታቻ ስርዓት ሊኖር እንደሚገባ አንድ ጥናት አመላከተ። ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት፤ ከ40-50 ዓመታት ውስጥም በኢንዱስትሪ ከበለጸጉ አገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጥረት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጉልህ ሚና እንዳለው ይታመናል። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በዓለም ገበያ ተወዳድረው ማሸነፍ እንዲችሉ አገር ውስጥ ያለውን ተነጻጻሪ ጉልበት፣ መሬትና ጥሬ እቃ በቴክኖሎጂ በመጠቀም ውጤታማና ምርታማ በሆነ አግባብ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በዚህም የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በአምራች ኢንዱስትሪ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ያሉ ተግዳሮቶች፣ ዕድሎችና የፖሊሲ አማራጮች ዙሪያ አውደ ጥናት አካሂዷል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተወካዩ አቶ ሙሉጌታ ውቤ ባቀረቡት ጥናት እንዳመላከቱት ጠንካራ የምርምርና ስርፀት ስራ የአገር ውስጥ የቴክኖሎጂ አቅምን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት ለማላመድ ይረዳል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማትን ለማፋጠን ለምርምርና ስርፀት ስራዎች ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል። በኢትዮጵያ 98 በመቶ የሚሆነው የምርምር በጀት ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የመንግስት ተቋማት የሚመደብ ነው። ይህም የግል ቢዝነስ አንቀሳቃሾች ምርምር ላይ እንዲሳተፉ የሚደረገው ጥረት አናሳ መሆኑን ያሳያል ሲል ጥናቱ ይጠቁማል። በአገሪቷ የግሉ ዘርፍ በምርምር ላይ ያለው አስተዋጽኦ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በዘርፉ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ከ142 የዓለም አገራት 133ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ስትሆን ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ዝቅተኛው ነው። በሌላ በኩል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተቋማት ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያላቸው ፍላጎት ማነስና የአገር ውስጥ ተቋማትም የቴክኖሎጂ አቅምን ከማሳደግ ይልቅ የዕለት ተዕለት ምርትን ብቻ ትኩረት ማድረጋቸው ለዘርፉ ችግር እየሆነ መምጣቱም በጥናቱ ተመላክቷል። አሁን ባለው የኢንቨስትመንት ህግ አንድ ባለሃብት ከውጭ ይዞት የሚመጣው ቴክኖሎጂ የሚገመገምበት አሰራር መዘርጋት እንዳለበትም ተጠቁሟል። በመሆኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኖሎጂ ልማት መበልጸግ ወሳኝ በመሆኑ በተለይ መንግስት በአምራች ኢንዱስትሪ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ስራዎችን በበቂ ሁኔታ የሚደግፍ የፋይናንስና የማበረታቻ ስርዓት ሊፈጥር እንደሚገባ አመላክቷል። የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ጥያሩ እደገለጹት ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት 71 ያህል የጥናትና ምርምር ስራዎች እያካሄደ ሲሆን 16ቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ይህም በተለይ ጉልበትን በሰፊው በሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ላይ በማተኮርና ካፒታልን በመቆጠብ ለኢንዱስትሪው ማንሰራራት መሰረት መጣል ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአንድ አገር ህልውና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይሁንና የቴክኖሎጂ ሽግግር ትርጉም፣ አረዳድና የግንዛቤ ክፍተት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር በአገር አቀፍ ደረጃ፣ በዘርፉና በተቋም በታቀደ መልኩ አለመሰራት በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ዙሪያ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮች ናቸው ብለዋል። በዘርፉ ያሉ አካላት ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂ አቅምና ተነሳሽነት ማነስ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስልቶች በአግባቡ አለመለየትና አለመጠቀም ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ምርምርና ስርፀት አለማጠናከርም እንዲሁ። በአውደ ጥናቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው መንግስት ምቹ ፖሊሲዎችን በመቅረጽና ብቁ ተቋማትን በመፍጠር ረገድ ጉልህ ድርሻ ሊኖረው ይገባል ብለዋል። በኢንዱስትሪ ልማትና በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ሂደትም ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አመልክተዋል። የልማት ኢንስቲትዩቶች፣ የዩኒቨርሲቲዎችና የአማካሪ ድርጅቶች ሚናም ከፍተኛ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል። በቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማትም የእያንዳንዱ ተዋናይ ሚና የሚለይበት ግልጽ የሆነ የህግ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባም ተገልጿል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል እ.አ.አ 2014 ባወጣው መረጃ ኢትዮጵያ ከሳይንሳዊ ምርምር ተቋማት ጥራት አንጻር ከዓለም 142 አገራት 93ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ደቡብ ኮርያ፣ ቻይና፣ ታይዋን፣ ጃፓን፣ ቬትናምና ጀርመን በቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት የበለጸጉ አገራት መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም