በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ዘመናዊ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ዘመናዊ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ ያስፈልጋል ተባለ
ጥቅምት 27 / 2012 በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ዘመናዊ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። የአፍሪካ ዝሆኖች መኖሪያ በሆነው የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ከሶስት ቀናት በፊት የእሳት አደጋ መከሰቱ ይታወቃል። አደጋው እስካሁን ባለው መረጃ በፓርኩ በሚኖሩ እንሰሳት ላይ ጉዳት ባያደርስም በመኖሪያ አካባቢያቸውና በሚመገቧቸው ዕጽዋት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ተጽእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር የፓርኩ ሃላፊ አቶ ዘነበ አረፋይነ ለኢዜአ ተናግረዋል። የቃፍታ ሽራሮ ብሄራዊ ፓርክ ሁለት ሺህ 147 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሽፍን ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንድ ሺህ 500 ሄክታር የሚሆነው የፓርኩ ክፍል ጉዳት ደርሶበታል ነው የተባለው። እሳቱን ለመቆጠጠር የአገር መከላከያ ሰራዊትአባላትን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ ሚሊሻ እና የትግራይ ልዩ ኃይል ርብርብ እያደረጉ ቢሆንም መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ምቹ ባለመሆኑ እሳቱን መቆጣጠር አለመቻሉን ሃላፊው አስታውቀዋል። ፓርኩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ኩራት በመሆኑ አደጋው ሳይዛመትና የከፋ ጉዳት ሣያደርስ ለመቆጣጠር ያስችል ዘንድ ዘመናዊ የእሳት ማጥፊያን መጠቀም እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል። የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን አደጋውን ተከትሎ ወደ ስፍራው የልዑካን ቡድን መላኩን ለማወቅ ተችሏል። ብሄራዊ ፓርኩ ከ50 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረና የአፍሪካ ዝሆኖች መኖሪያ መሆኑ ይነገርለታል። ባለፈው ዓመት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተከስቶ የነበረውን የእሳት አደጋ ከእስራኤል በተገኘ ድጋፍ መቆጣጠር መቻሉ የሚታወስ ነው።