ቀጥታ፡

የአፋር ክልል ያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክን የማስተዳደር ኃላፊነት ሊረከብ ነው

ጥቅምት 27/2012 የያንጉዲራሳ ብሄራዊ ፓርክን ለአፋር ክልል ለማስረከብ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣ አስታወቀ። በርክክቡ ዙሪያ ባለስልጣኑ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሰመራ ከተማ ውይይት ዛሬ አካሂዷል። በዉይይቱ ላይ የባለስጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን እንደተናገሩት ከሀገራችን 27 ብሄራዊ ፓርኮች ውስጥ በአፋር ክልል የሚገኘው ያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክ 4ሺህ 730 ስኩዌር ኪሎሜትር ቦታ ላይ የሰፈረ ነው። በአፋር ክልል በገዋኔና በሜሌ ወረዳዎች መካከል የሚገኘው ብሔራዊ ፓርኩ በ1977 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በውስጡም የሜዳ አህያ፤ ሳላና የሜዳ ፍየሎችን ጨምሮ የተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎችን የያዘ ነው። ይሁንና ፓርኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የእንስሳት ግጦሽ ፣ህገ-ወጥ አደንና ሰፈራ በስፋት በመከናወኑ የፓርኩን ህልውና አደጋ ውስጥ ጥሎታል። "ችግሩን ለማቃለልም ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ በአፋር ክልል እንደመገኘቱ ምንም አይነት የይገባኛል ጥያቄ የሌለበት በመሆኑ በክልሉ ስር ቢተዳደር የተሻለ ጥበቃና በህብረተሰቡም ዘንድ የባለቤትነት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል ስለታመነበት ለክልሉ ለማስተላለፍ ባለስልጣኑ ወስኗል" ብለዋል። ፓርኩን ለክልሉ ለማስተላለፍ በተደረጉ ተደጋጋሚ ምክክሮችም መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸው "በዚህ ሳምንት ከክልሉና ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተወጣጡ ሰባት አባላት ያለው ኮሚቴ ተዋቅሮ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ሙሉ ለሙሉ ርክክቡን ለማስፈጸም እየሰራ ነዉ" ብለዋል። የአፋር ክልል ምክትል ርእሰ-መስተዳድር አቶ ኡስማን መሃመድ "ለፓርኩ እዚህ ደረጃ መድረስ የክልሉም ሆነ የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የራሳቸዉ ደርሻ አላቸዉ"ብለዋል። በተለይም በክልሉ በአመራሩና በህብረተተሰቡ ዘንድ በፓርኩ ላይ የባለቤትነት ስሜት በሚፈለገው ደረጃ አለመዳበር እያደረሰ ላለዉ ጉዳት በምክንያትነት ተጠቃሽ መሆኑን አስረድተው የአፋር አርብቶ አደር ህብረተሰብ ስለአካባቢ ጥበቃ ያለው ባህላዊ እሴት ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል። ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶችንና የዱር እንስሳቱን ጠብቆና ተንከባክቦ በማልማት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ በመፍጠር ያንጉዲራሳ ብሄራዊ ፓርክን አሁን ከተደቀነበት አደጋ ለማትረፍ ክልሉ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። ለዚህም የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣንም ፓርኩን ለክልሉ አስረክቤያለሁ ብሎ ከመደገፍ ሳይታቀብ በጋራ በመስራት አሁን ካለበት ሁኔታ ለማላቀቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ አሊ መሃመድ በበኩላቸው በፓርኩ አካባቢ የነበሩ ሁለትና ሶስት መንደሮች በሂደት እያደጉና ሌሎችንም እየተጨመሩ አካባቢው መደበኛ የመኖሪያና የከብቶች መዋያ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል። ፓርኩ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በአጭር ገዜ ዉስጥ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፋና የዱር እንስሳቱም ሊሰደዱ ስለሚችሉ የክልሉ መንግሰት ጣልቃ በመግባት አስፈላጊውን ጥበቃና አንክብካቤ በማድረግ ፈጥኖ እንዲያገግም አንደሚሰራ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም