ለሙያ ስነ-ምግባር ያልተገዙ መገናኛ ብዙሃን ግጭቶች እንዲስፋፉ እያደረጉ ነው - ጋዜጠኞች - ኢዜአ አማርኛ
ለሙያ ስነ-ምግባር ያልተገዙ መገናኛ ብዙሃን ግጭቶች እንዲስፋፉ እያደረጉ ነው - ጋዜጠኞች
ጥቅምት 27/2012 አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የሙያውን ስነ-ምግባር ተከትለው ባለመስራታቸው በአገሪቷ የሚከሰቱ ግጭቶች እንዲባባሱ እያደረጉ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ጋዜጠኞች ተናገሩ። በፕሮግራሞቻቸውና በዜና ሽፋኖቻቸው ለብሔር አጀንዳ ትኩረት እየሰጡ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ለሙያ ስነ-ምግባራቸው ባለመወገናቸው አገሪቷን ለቀውስና ለችግር እያደረጓት ነው ይላሉ ጋዜጠኞቹ። በኢትዮጵያ በተለይም ብሔር ተኮርና የፖለቲካ ወገንተኛ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ትተው ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት ስራቸው እስኪመስል እየሰሩ ነው የሚሉ አስተያየቶችም ይነሳሉ። ይህን ሃሳብ የሚጋራው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ጌትነት አንዳንድ ሚዲያዎች ለአንድ ወገን አስተሳሰብ፣ የፖለቲካ ፍላጎት እና የብሔር አጀንዳ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ከሙያው ስነ-ምግባርም እየራቁ ነው ይላል። ብሔርን ከብሔር፣ ሐይማኖትን ከሐይማኖት የሚያጋጩ አጀንዳዎችን እያነሱ አሁን በአገሪቷ የተከሰተው ቀውስ እንዲባባስ አስተዋጽኦ እያደረጉ በመሆኑም ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጿል። ጋዜጠኛ ተስፋዬ መንግስት መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባራቸውን አክብረው እንዲሰሩ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ብሏል። የአሐዱ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠም ሚዲያው ስነ-ምግባርን በተከተለ መልኩ ብቻ መስራት አለበት ይላል። አሁን በአገሪቷ ያለውን የግጭት ሁኔታ ጨምሮ ሁሉንም ጉዳይ እንዴት መዘገብ እንዳለባቸው በሙያው ስነ-ምግባር የተቀመጠ በመሆኑ ይህን ቢያደርጉ ለአገር የሚጠቅም ስራ መስራት እንደሚቻልም ተናግሯል። አንዳንድ ሚዲያዎች ከፍተኛ ጥፋትና ኪሳራ እያደረሱ መንግስትንም እየተገዳደሩ መጥተዋል ያለው ጋዜጠኛ ጥበቡ ይህን የሚያደርጉ አክራሪ የሚዲያ ኃይሎች ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው ብሏል። ‘’በዘር፣ በማንነትና በቋንቋ ፖለቲካ የተገነባች አገር ውስጥ ሚዲያውም ይህንኑ ማስተጋባት በእሳት ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ ነው አደጋውም የከፋ ይሆናል’’ ነው ያለው። በአዲሱ የሚዲያ ህግ ረቂቅ መሳተፉን የተናገረው ጋዜጠኛ ጥበቡ ''ይህ ሕግ ለሚዲያው ኢንዱስትሪ ጠቃሚ በመሆኑ በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግ አሁን ላለው ችግር መፍትሔ ይሆናል'' በማለት ገልጿል። በአዲሱ ህግ ከተካተቱት ነጥቦች ከዘር፣ ከቋንቋ፣ ከሐይማኖትና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሲሆን በሕዝቦች መካከል ልዩነት የሚፈጥሩ ሚዲያዎች እንዳይኖሩም ያግዳል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከሰሞኑ የሩብ ዓመት ሪፖርቱን ለሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ መስመር የሳቱ ሚዲያዎችን ወደ መስመር ለማስገባት በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት አልተወጣም የሚል ወቀሳ ደርሶበታል። ባለስልጣኑ እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክር ለማስፈራራት የሚሞክሩ ወገኖች እንዳሉ የገለጹት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ጥንቃቄ በተሞላበት፣ በሆደ ሰፊነትና በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት ተጠያቂ ለማድረግ እንደዘገየ ተናግረዋል። ከህግ ውጭ የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ተቋማት በሕጉ ድንጋጌ መሰረት ጣቢያ እስከመዘጋት ተጠያቂ ይሆናሉም ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የባለስልጣኑን ኃላፊነትም ሆነ የሚዲያ ተጠያቂነትን ያሰፍናል የተባለውና የተሻሻለው የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ገልጸዋል።