ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አገር በቀል ዕውቀትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ የማዋል ውስንነት አለባት ተባለ

ጥቅምት 27/2012 አገር በቀል ዕውቀትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። ኢትዮጵያ ለዓለም የሚበቃ ጥልቅ አገር በቀል ዕውቀት ያለባት አገር ብትሆንም ሳይንስ ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ በበቂ ደረጃ አልተጠቀምንበትም ተብሏል። የሳይንስ ሳምንት በኢትዮጵያ "ሳይንስ ለልማትና ለብልጽግና" በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 25 እስከ ህዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተካሄደ ነው። ዛሬም የሳይንስ ሳምንቱ አካል በሆነው መርሃ-ግብር ከሙያ ማህበራትና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር ምክክር ተደርጓል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፈሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፤ ሳይንስ ከሰው ልጆች መፈጠር ጋር አብሮ የተፈጠረ ነው። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት ሲባል ድንጋይ በማሾል፣ እንጨት በመቁረጥ መሳሪያ በመጠቀም የሳይንስ ጀማሪ ናት ማለት ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ ያለንን አገር በቀል ዕውቀት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ባለመቻላችን አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሰረት መገንባት ተስኖናል ብለዋል። ጀርመን አይበገሬ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ስትፈጥር፤ ጃፓን ለአየር ንብረት ተጽዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚ ስትገነባ መነሻቸው ሳይንስ መሆኑን ጠቁመዋል። ቻይና በዓለም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያስመዘገበችው፤ አሜሪካ የዓለም 24 በመቶ የሆነውን ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ያስመዘገቡት ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ትኩረት በመስጠታቸው መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያም ጠንካራ መሰረት ያለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ለማምጣት አገር በቀል ዕውቀትን ሳይንሳዊ መሆነ መንገድ መጠቀም አለባት ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ከአሜሪካ፣ ቻይናና ጃፓን ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት በቅርበት ውይይት ማድረግ መጀመራቸውን ገልጸዋል። በቅርቡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የአገር በቀል ዕውቀት ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ምክክር ተደርጓል። የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በመተባበር አገር በቀል ዕውቀትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲያወሉት መሰረት ተጥሏል ነው ያሉት። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ስራው ውጤታማ እንዲሆን ለተቋማቱ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም