ቀጥታ፡

ሶስቱ አገራት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ተወያይተው የጋራ አቋም መግለጫ ወጥቷል

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2012 የኢትዮጵያ የሱዳንና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ዋሽንግተን ላይ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተወያዩ በኋላ የጋራ አቋም መግለጫ ወጥቷል። የአቋም መግለጫውን ያወጡት ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ አሜሪካና የዓለም ባንክ በጋራ  በመሆን ነው። የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቴቨን ሙንቺን እና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ በተገኙበት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ ውይይት አካሂደዋል። ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በተመራ የልዑካን ቡድን በውይይቱ ተሳትፋለች። ውይይቱን ተከትሎም የጋራ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሶስቱ አገራት እ.አ.አ 2015 በካርቱም በተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት መሰረት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና ግንባታ ላይ ሁሉን አቀፍ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ፣ ትብብር ላይ የተመሰረተና ዘላቂነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስና ግልጽ የውይይት ሂደት ለመዘርጋት ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን የአቋም መግለጫው ያመላክታል። በዚሁ መሰረት የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ አራት የቴክኒክ ውይይቶች ለማካሄድ ከስምምነት ደርሰዋል። በውይይቶቹ ላይ አሜሪካና የዓለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት እንዲሳተፉ ሚኒስትሮቹ መስማማታቸውን የጋራ አቋም መግለጫው ያሳያል። በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው የቴክኒክ ስብሰባ ህዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ታውቋል። ሚኒስትሮቹ ስምምነቱ እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያልቅ እና ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም እና ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን በህዳሴ ግድቡ ላይ በሚካሄደው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በመገኘት ስምምነቱ የደረሰበትን ለመገምገምና የውይይቱን ሂደት ለመደገፍ ተስማምተዋል። ሶስቱ አገራት እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ስምምነት ላይ ካልደረሱ እ.አ.አ ካርቱም ላይ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንዲሆን መስማማታቸውን የአቋም መግለጫው ያመለክታል። የካርቱም የመርሆዎች ስምምነት 10 አንቀጾች የያዘ ነው። የመጨረሻው አንቀጽ 10 ሶስቱ አገራት በመርሆዎች ስምምነቱ አተረጓጎምና ተግባራዊነት የተነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ወይም በድርድር ይፈታሉ። አገራቱ በመርሆዎች ስምምነት ላይ ያላቸውን አለመግባባት በውይይት ወይም በድርድር መፍታት ካልቻሉ አደራዳሪ ሊጠይቁ ወይም ለአገራቸው ርዕሳነ ብሔሮችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሊያሳውቁ ይችላሉ ይላል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ፣ ለሱዳንና ለግብጽ ህዝቦች ልማት ያለውን ጠቀሜታና ድንበር ተሻጋሪ ትብብር ያለውን ጠቀሜታ አጽንኦት ሰጥተው በህዳሴ ግድቡ ላይ በተባለው የጊዜ ገደብ ከስምምነት ለመድረስ ያላቸውን የጋራ ፍላጎት መግለጻቸውንም የአቋም መግለጫው ያመለክታል። በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የተደረጉ ገንቢ ውይይቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለሶስትዮሽ የቴክኒክና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት አለመቀጠል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች በዝርዝር መቅረባቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊና ሚዛናዊ የውሃ መብት እንዳላት በውይይቱ ላይ ማስገንዘቧንም አምባሳደሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሹን የቴክኒክ ውይይት ለመቀጠል ከስምምነት ላይ መደረሱ እንዳስደሰታቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም