ቀጥታ፡

ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ለሚፈጠረው የአገልግሎት ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል-ደንበኞች

ድሬዳዋ ጥቅምት 27ቀን 2012 ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ለሚፈጠረው የቴሌኮም አገልግሎት ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግለት የድሬዳዋ ደንበኞች ጠየቁ።

የምስራቅ ሪጅን ኢትዮ-ቴሌኮም ድሬዳዋ ከሚገኙ ኢንተርፕራይዝ ደንበኞች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ተገልጋዮች ጋር በተወያየበት ወቅት አገልግሎት ሰጪዎቹ የሪጅኑ  የሥራ እንቅስቃሴ ከኤሌክትሪክ ጋር የተገናኘ በመሆኑ አስተማማኝ አገልግሎት ለማግኘት መፍትሄ ሊፈልግለት ይገባል ብለዋል።

ከአገልግሎት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ሰለሞን ታዬ ተቋሙ ''ኤሌክትሪክ ሲጠፋ ተጠባባቂ ጄኔሬተር ማዘጋጀት አለበት፡፡''

በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት የሚላኩ አጭር የፅሁፍ መልዕክቶች ባለቤቱ ጋር ሳይደርሱ አየር ላይ ስለሚቀሩ  መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

ሌሎች ደንበኞች በበኩላቸው ኢትዮ -ቴሌኮም የኢንተርኔት መቀበያ ሣጥን /ዲ ኤስ ኤል/፣ የሞባይልና  መደበኛ ስልክ ቀፎዎች በበቂ መንገድ ማቅረብ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪ በግል ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው የሚመጡ የማይፈልጓቸው መልዕክቶች  ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የኢንተርኔት ማስተላለፊያ የሆኑ የፋይበር ገመዶች ለሥራ ምቹነት በሌለው መንገድ ባለመዘርጋታቸው በከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እየተበጠሱና ለስርቆትም እየተዳረጉ በመሆኑ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ቴሌ፣ ኤሌክትሪክ፤ ውሃና ፍሳሽ የመሣሰሉት ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዘዴ ቢፈፅሙ ጊዜና ጉልበትን መቆጠብ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

የምስራቅ ሪጅን ኢትዮ-ቴሌኮም ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ጣሰው ሽመልስ የተሰጡ ጥቆማቸውን በሙሉ በዕለት ተዕለት ሥራ ውስጥ በማካተት መፍትሄ ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

ከኢትዮ-ቴሌኮም ማሽን፤ ከሞባይል ባንኪንግና ከአጭር የባንክ አገልግሎት ጽሁፎች ጋር ተያይዘው የተነሱ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመለየት በፍጥነት መፍትሄ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡

ሁሉን አቀፍ የኢትዮ-ቴሌኮምን አገልግሎቶች በሙሉ ከሚሰጡ 59 ሳጥኖች ለ42ቱ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ አገልግሎት እንዲሰጡ ጄኔሬተር ተገጥሞላቸዋል።

ቀሪዎቹ ሣጥኖች የሚያስተናግዷቸው ደንበኞች ብዛት እየታየ በአጭር ጊዜ መፍትሄ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም