ገናሌ ዳዋ ሶስት ኃይል ማመንጨት ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ገናሌ ዳዋ ሶስት ኃይል ማመንጨት ሊጀምር ነው
ጥቅምት 27/2012 የገናሌ ዳዋ ሶስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከሁለት ወር በኋላ ማመንጨት ይጀምራል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ አብዛኛው ስራ ተጠናቋል። የኃይል ማመንጫው ግድብ ውሃ የሞላ ሲሆን ዋና ዋና የሙከራ ስራው ተጠናቆ አፈጻጸሙ ከ99 በመቶ በላይ ደርሷል። እንደ ዶክተር አብርሃም ገለጻ 254 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ፕሮጀክቱ ቀሪ የሙከራ ስራው እንደተጠናቀቀ ከሁለት ወር በኋላ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ። ግንባታው በ2003 ዓ.ም የተጀመረው የገናሌ ዳዋ ሶስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በካሳ ክፍያ ሳቢያ ለሶስት ዓመታት ስራው ተቋርጦ ነበር። በተጠናቀቀው የ2011 በጀት ዓመት ችግሩን በመፍታት ፕሮጀክቱን የማፋጠን ስራ መከናወኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት። ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ኃይል ማንጨት ሲጀምርም አሁን ከ4 ሺህ 260 በላይ ሜጋ ዋት የሆነውን የአገሪቷን የኃይል አቅርቦት እንደሚያሳድገው ይጠበቃል። ፕሮጀክቱ በ451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር አብርሃም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ 22 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በስራ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። አይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ መልካ ሰዲያ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ፣ ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫና የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ በግንባታ ላይ የሚገኙ ናቸው። በ2012 የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት 3 ሺህ 541 ነጥብ 34 ጌጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል መመረቱንም የተቋሙ መረጃ ያመለክታል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የአምስት በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል። በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ ከአገር ውስጥ ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎችና ከአገር ውስጥ ሽያጭ 1 ነጥብ 59 ቢሊዮን ብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን አፈጻጸሙም 96 በመቶ ነው ተብሏል።