ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጠናዊ ውህደት ወሳኝ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጠናዊ ውህደት ወሳኝ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ
ጥቅምት 26 ቀን 2012 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደት የሚኖረው ሚና ወሳኝ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።
ኢዜአ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በቀጠናዊ ትስስር ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙሪያ የኢኮኖሚ እና የውሃ-ፖለቲካ ምሁራንን አነጋግሯል።
የኢኮኖሚ ባለሙያና የኦሮሚያ የፕላንና የኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ተሾመ አዱኛ ዋና የሚባሉ የቀጠናዎች ስኬቶች መሰረት በውህደትና በትብብር ላይ ባደረጉ ቋሚ የጋራ ምክክር መድረኮች መሆኑን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩ ገልጸዋል።
"የእነዚህ ስኬቶች መሰረት የሆነው አዝማሚያ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሊኖር እንደሚገባና ይህን ቀጠናዊ ትስስር እውን የሚያደርጉ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ" ብለዋል ዶክተር ተሾመ።
በአፍሪካ ቀንድ ብዙ ያልተጠቀምንባቸው ሀብቶች አሉ የሚሉት ባለሙያው እነዚህም ሀብቶች ለቀጠናዊ ውህደት መጠቀም ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ ካላቸው አገራት አንዷ ስትሆን በቀጠናው የሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል እንደሆነች አንስተዋል።
"የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ የምታራምዳቸው ሀሳቦች በዓለም ደረጃ ለውህደት ምሳሌ መሆን የሚችል ነው" ሲሉ አክለዋል።
ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ ጸጋዎች ውሃ ዋንኛው በመሆኑ ይህንኑ በኢኮኖሚ የልማት ኮሪደሯቿ ተነጻጻሪ ጥቅሟን መሰረት አድርጋ የማልማት መብት እንዳላት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ እምቅ ሀብቶች ቢኖሯትም በብዙ ምክንያቶች አሁንም "ድሃ" ከሚባሉት አገራት አንዷ እንደሆነች ይሄም ካላት የውሃ ሀብት አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።
"እኛ ትክክል የሆነ የውሃ አስተዳደርና የውሃ ማጠራቀሚያ የለንም ስለዚህም አግባብ የሆነ የውሃ አስተዳደር አማራጭ የሌለው ነው።" ሲሉ ዶክተር ተሾመ ገልጸዋል።
የመንግስት ባለፉት ዓመታት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ካደረጋቸው ጉዳዮች አንዱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያና በቀጠናው አገራት ያሉ ህዝቦችን ህይወት ለመቀየር ይረዳል ብለዋል።
ለህዳሴ ግድቡ እውን መሆንና ለግንባታ ስራው መንግስት የቅኝ ግዛት ህጎችን ሳይሆን ትብብርን የሚደረግፉ ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት አድርጎ ምላሽ መስጠትና እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንኛ አላማ የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ድህነትን መቀነስ እንጂ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ለመጉዳት እንዳልሆነ ሊታወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
መንግስት በህዳሴ ግድቡ የትኩረት አቅጣጫው ሃይል ማመንጨትና የአባይ ወንዝ ውሃው ባለበት ሁኔታ መፍሰሱ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሆነም ነው ዶክተር ተሾመ ያስረዱት።
የኢትዮጵያ መንግስት ዓለም አቀፍ ህግን መሰረት አድርጎ ከሆነ ኢትዮጵያ ማንም መካድ የማይችለው ውሃን የመጠቀም የተፈጥሯዊ መብት እንዳላት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የግድቡ ግንባታ እውን እንዲሆን ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የውሃ-ፖለቲካ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድንና ጎረቤት አገራቶችን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ቁልፍ አገር ናት ብለዋል።
ቀጠናዊ ውህደቱ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዋነኛ ማእከል እንደሚያደርጋትም ጠቅሰዋል።
የሃይል እጥረት በአፍሪካ አንገብጋቢ ችግር እንደሆነና በሃይል መተሳሰር ለቀጠናው ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለገበያ ትስስር ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ውህደቱ ወደ ጋራ ገበያ የመቀየር እድል እንዳለውና ይሄም የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የመሰሉ ቀጠናዊ ተቋማትና ሌሎችም አቅማቸውን እንዲጠቀሙ እንደሚያግዛቸው ነው ዶክተር ያዕቆብ ያስረዱት።
አሁን ያለው ሁኔታ በቀጠናው አገራት ያለው የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ ብዙ ጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚፈልጉም አክለዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመነሻ እቅድ የግድቡን የኤሌክትሪክ ሃይል ከጎረቤት አገራት አልፎ ለሳዑዲ አረቢያ፣ ጆርዳን፣ ቱርክና የሰሜን አፍሪካ አገራት ትኩረት ያደረገ ሽያጭ እንደምታደርግ ያስቀምጣል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲሆን በአሁኑ ሰአት የገድቡ ግንባ ሂደት 68 ነጥብ 5 በመቶ ላይ ደርሷል።
ኢትዮጵያ ብዙ የውሃ ሀብት ካላቸው የአፍሪካ አገሮች መካካል ግንባር ቀደም ብትሆንም እስካሁን በአግባቡ አልተጠቀመችበትም።
የውሃ ሀብቷ በ8 ዋና ገባር ወንዞች የተሰራጨ ሲሆን 45 ሺህ ሜጋዋት የኤሌትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳለውም መረጃዎች ያመለክታሉ።