ለዘላቂ ሰላም የጥፋት ኃይሎችን በማጋለጥ ከመንግስት ጋር እንሰራለን--- የያቤሎ ከተማና አካባቢው ሴቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለዘላቂ ሰላም የጥፋት ኃይሎችን በማጋለጥ ከመንግስት ጋር እንሰራለን--- የያቤሎ ከተማና አካባቢው ሴቶች
ነገሌ/ጅማ (ኢዜአ) ጥቅምት 26 ቀን 2012 ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም የጥፋት ኃይሎችን በማጋለጥ ከጸጥታ ኃይል ጋር ተባብሮ ለመስራት መዘጋጀታቸውን በቦረና ዞን የያቤሎ ከተማና አካባቢው ሴቶች ገለጹ።
የጅማ ከተማ ወጣቶች በበኩላቸው የአካባቢያቸው ሰላም እንዲጠበቅና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል፡፡
የያቤሎ ከተማና አካባቢው ሴቶች ይህን ያሉት ዛሬ በያቤሎ ከተማ ለሴቶች ብቻ በተዘጋጀ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው ነው።
የያቤሎ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አሀዶ አብዱረህማን ከጊዜ ወደ ጊዜ የብሔር መልክ እየያዘ የመጣው ግጭት የአገሪቱን ገጽታ እያበላሸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ህጻናትና ሴቶችን ጭምር የጉዳት ሰለባ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
በመብት ጥያቄ ሽፋን ህዝብ ከህዝብ በማጋጨት ስራ የተጠመዱና አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሰሩ የጥፋት ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ወይዘሮ አሀዶ ጠይቀዋል፡፡
በከተማቸው የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ አጥፊዎችን በማጋለጥ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ሌላው የሰላም የኮንፈረንሱ ተካፋይ ወይዘሮ ስመኝ ባልቻ በኦሮሚያ ክልል በብሔርና በሃይማኖት ሽፋን በሰው ህይወት ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡
በግጭት አገር ከማፍረስ በቀር አሸናፊም ተሸናፊም ስለማይኖር በተለይ ወጣቶች ቆም ብለው እንዲያስቡ ነው የመከሩት፡፡
ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት በተለያዩ ሚዲያዎች የሚነገሩ የጥላቻ ቅስቀሳዎችን ለማስቆም መንግስት ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡
ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ በአጥፊዎች ተገፋፍቶ የሰው ሕይወት ከማጥፋት፣ ንብረት ከማቃጠልና አገሩን ሊጎዳ ከሚችል ተግባል ሊቆጠብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
"የመረዳዳት፣ የመተሳሰብና የመቻቻል ባህላዊ እሴቶችን ወደጎን በመተው በአንዳንድ ሚዲያዎች እየተነገረ ያለው የጥላቻ ቅስቀሳ በህግ ሊገደብ ይገባል" ያሉት ደግሞ የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት መቅደስ ተፈራ ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን ተፈጥሮ በነበረ ሁከትና ብጥብት የሰው ሕይወትና ንብረት የጠፋው በዚሁ የጥላቻ ቅስቀሳ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
"የኦሮሞ ህዝብ አቃፊነት፣ እንግዳ ተቀባይነትና የመረዳዳት ባህላዊ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሴቶች ከሚመለከተው አካል ጋር ተባብሮ መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡
ኮንፈረንሱን የመሩት የያቤሎ ከተማ ከንቲባ አቶ ጃተኒ ሶራ እናቶች የልጆቻቸውን ስነ ምግባር በመጠበቅ የሰላምና የሀገር ገጽታ ግንባታ አምባሳደር እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
"መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከጥላቻ፣ ቂምና በቀል የጸዳ አገራዊ አንድነትንና የህዝብ ተሳትፎ ይፈልጋል" ሲሉም አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የአካባቢያቸው ሰላም እንዲጠበቅና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የጅማ ከተማ ወጣቶች ጠይቀዋል፡፡
የከተማው ወጣቶች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ ዛሬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ተካሂዷል፡፡
በኮንፈረሱ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች የከተማው ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የወጣቱን ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከወጣቶች መካከል አቡዱ ከደር በጅማ ከተማ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ገልጾ አስተማማኝ ሰላም በከተማው ለማስፈን ወጣቱን ከሱሰኝነት መከላከልና ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገ ተናግሯል።
ሌላዋ ወጣት አሚና አባቆሮ "የጅማ ከተማ ወጣቶች ለሰላም መደፈረስ ሲጋለጡ የሚታየው ሥራ አጥ በመሆናቸው ነው" ብላለች፡፡
በቀጣይም ሰላም እንዲረጋገጥ መንግስት የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ከግል ባለሃብቱና ከሌሎች አካላት ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበት ጠቁማለች፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሃመድ በጅማ ከተማ በቅርቡ የጸጥታ መደፍረስ ቢያጋጥምም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የአገር ሽማግሌዎች፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አባገዳዎች ያደራጉት ጥረት የጎላ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
በቀጣይም መሰል ችግሮች እንዳይጋጥሙ መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራ በመንግስት ብቻ ሳይሆን በወጣቶቹ በኩል የቁርጠኝነት ችግር መኖሩን አንስተዋል፡፡
የኦሮሚያ ኢንትርፕራይዝና እንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ በበኩላቸው ወጣቶች አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በሰከነና በተረጋጋ መንገድ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስረድተዋል።
መንግስት በአገሪቱም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የሚታዩ የወጣቶች የሥራ እድል ፈጣራ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡