ቀጥታ፡

በአገሪቷ ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲፈቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ምክር ቤቱ ገለጸ

ጥቅምት 26/2012 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ባልተፈቱ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ የሰላም ሚኒስቴር በሚያቀርባቸው ዝርዝር መረጃዎች መሰረት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ። የሰላም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የ2012 በጀት ዓመት ዕቅዱን ለምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ፤ በፖለቲካ አመራሩ ዘንድ በተለያዩ የፀጥታ አካላት ላይ የሚታዩ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ለምክር ቤቱ ዝርዝር መረጃዎች ሊቀርብለት ይገባል ብለዋል። በተለይ በህዝብ ሰላምና ደህንነት ላይ ችግር የሚፈጥሩ የፖለቲካ አመራሮች ፊት ለፊት ተገናኝተው ውይይት ሊያደርጉ ይገባልም ነው ያሉት። በአገሪቷ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያደናቅፍ አመራር ሲያጋጥም የሰላም ሚኒስቴር ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ብለዋል። ምክር ቤቱም ከሰላም ሚኒስቴር የሚቀርቡለትን መረጃዎች መሰረት በማድረግ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አረጋግጠዋል። ''በአገሪቷ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የከፋ ደረጃ ላይ ያልደረሰው በህዝቡ የመቻቻል ባህልና በፀጥታ ኃይሉ ጥንካሬ መሆኑን ምክር ቤቱ ይገነዘባል'' ብለዋል። በአንዳንድ ክልሎች የፀጥታ አካላት ዘንድ የሚታየው ''እኔ እበልጥ'' የሚለው ፉክክር "አገሪቷን የማትወጣው ትርምስ ውስጥ" ሊከታት ስለሚችል ምክር ቤቱ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ዕድል ሊሰጠው እንደሚገባም ነው  አቶ ተስፋዬ የተናገሩት ። የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴሩ የግጭቱ መነሻ ናቸው ባላቸው ጉዳዮች ላይ ጊዜ ወስዶ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል። በኢትዮጵያ ለተፈጠረው የሰላም እጦት አይነተኛ ምክንያት የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄና የመዋቅራዊ ችግር መሆኑንም ጠቅሰዋል። በአገሪቷ ሰላም ለማሰፈን በሚደረጉ ጥረቶች ላይ እያጋጠመ ያለው ችግር ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ሲሆን በተለይ አመራሩ የግል ፍላጎቱን የማስቀደም ዝንባሌ በስፋት እንደሚታይም አስረድተዋል። ''ፖለቲከኞች በሰከነ ስሜት ከግል በላይ አገር፣ ከራስ በላይ ህዝብ ብሎ መቆም ይጠይቃል'' ያሉት ሚኒስትሯ ለሰላም መስፈን ሁሉም እኩል መቆም እንዳለበት ገልጸዋል። በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስም ከህዝቡ ፍላጎት የመነጫና የሁለቱም ክልል ህዝቦች የማይቀበሉት መሆኑን አስረድተዋል። ይልቁንም በፖለቲካ አመራሩ ዘንድ ተቀራርቦ ለመነጋገር ፍላጎት በማጣት ምክንያት የሚፈጠር ችግር መሆኑን ገልጸዋል። የሰላም ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በሰላም ዙሪያ ለህዝቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት መሆኑን ወይዘሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል። ''በየደረጃው ያሉና ራሳቸውን ብቻ በማዳመጥ ሰላምን የማይሹ የፖለቲካ አመራሮችን ህዝቡ፣ ሰላሜን ስጡኝ፣ አልቀበላችሁም እንዲላቸው እንፈልጋለን'' ብለዋል። ከፖለቲካ አመራሮች ጋር ብቻ ውይይት በማድረግ መቀጠል የማይቻል በመሆኑ ህዝቡ አስተማማኝ የሰላም ኃይል ስለሆነ በሰላም ዙሪያ የማንቃት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት የሰላም ችግሮች ሳይፈቱ በቆዩባቸው የጉጂና የአማሮ፣ የቡርጂና የጌድኦ፣ የመስቃንና የማረቆ፣ የአማራና የቅማንት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ፣ የኦሮሚያና የሱማሌ እንዲሁም የአማራና የትግራይ አካባቢዎች ሰላም ለማስፈን ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ነው።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም