ቀጥታ፡

አየር መንገድና ንግድ ባንክ የጋራ ዘመናዊ የክፍያ አማራጭ ስርዓት ዘረጉ

አዲስ አበባ ኢዜአ/ ጥቅምት 26/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድና ንግድ ባንክ ዘመናዊ የክፍያ አማራጮችን መጠቀም የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋታቸውን አስታወቁ።

ሁለቱ ተቋማት የጉዞ ትኬቶችን ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ የክፍያ አማራጮችን መጠቀም የሚያስችል አሰራር መዘርጋታቸውን ያስታወቁት ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደገለጹት፤ ተቋማቱ አገልግሎታቸውን በማሳደግ ከጥሬ ገንዘብ ልውውጥ ባሻገር በዲጂታል ክፍያ ስራ በጋራ እየሰሩ ነው።

አየር መንገዱ 40 በመቶ የሚሆነውን የሽያጭ አገልግሎቱን ዲጂታል ያደረገ ሲሆን በአስር ወራት ብቻ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭ ማካሄዱን ገልጸዋል።

ይህም የደንበኞችን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ከማስቻሉ ባሻገር ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተነግሯል።

ተቋማቱ የትብብር ግንኙነታቸውን በማጠናከር በአሁኑ ወቅት "የፕላቲኒየም ኮ ብራንድድ ካርድ" አገልግሎት መጀመራቸውንም ይፋ አድርገዋል።

ይህ አገልግሎት ደንበኞች ወደተለያዩ አገራት ለመሄድ ወደ ትኬት ቢሮዎች መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሆነው መግዛትና ክፍያ መፈጸም እንዲሁም የምዝገባና ሌሎች አገልግሎቶችንም መጠቀም የሚያስችላቸው ነው።

አየር መንገዱ እነዚህንና ሌሎች ዘመናዊ አገልግሎቶችን በማጠናከር በአገሪቱ ቱሪዝምና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን እንደሚያከናውን በመግለጫው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚደንት አቶ ባጫ ጊና እንደገለጹትም ባንኩ 22 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።

አሁን ላይ ከሚሰጠው የግብይት አገልግሎት 30 በመቶው ዲጂታል ሲሆን በ2025 ይህን አገልግሎት 90 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚተገበረው "የፕላቲኒየም ኮ ብራንድድ ካርድ" አገልግሎት ደንበኞችን ከመጥቀም ባሻገር የባንኩን ቴክኖሎጂ የመተግበር አቅም ለማስፋት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ73 ዓመት ዕድሜው 125 ዓለም አቀፍ እና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት።

ከ77 ዓመታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በአገር ውስጥ 1 ሺ 516 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን በደቡብ ሱዳንና ጅቡቲም ቅርንጫፎች በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም