ቀጥታ፡

በተማሪዎች ላይ የማሳከክና ራስን የመሳት ጉዳት ደረሰ

ጥቅምት 26/2012 ነቀምቴ ኢዜአ ...... በምእራብ ወለጋ ዞን የኢናንጎ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማሳከክና ራስን የመሳት ጉዳት እንደደረሰባቸው የላ አሳቢ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ፅህፈት ቤት ገለፀ ፡፡ የጽህፈት  ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋ በቀለ እንደገለፁት ተማሪዎቹ ትናንት ጧት ትምህርታቸውን ለመከታተል እንደገቡ በሶስት  የመማሪያ ክፍሎች የነበሩ ተማሪዎች  ማሳከክ እንደጀመራቸውና ቀስ በቀስም ራሳቸውን የመሳትና የመውደቅ ሁኔታዎች እንዳጋጠማቸው ገልፀዋል፡፡ ጉዳት ከደረሰባቸው 42 ተማሪዎች መካከል 35ቱ ሴት ተማሪዎች ወዲያውኑ  ወደ ኢናንጎ ጤና ጣቢያ ቢወሰዱም የጤና ጣቢያው ተማሪዎቹን ወደ ግምቢ አጠቃላይ ሆስፒታልና ግምቢ አድቬንቲስት ሆስፒታሎች እንዲላኩ አድርጎአቸዋል ። የግምቢ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ደሣለኝ አበበ እንደገለፁት  15 ተማሪዎች በግምቢ አድቬንቲስት ሆስፒታል 28 ተማሪዎች ደግሞ በግምቢ አጠቃላይ ሆስፒታል ተኝተው ህክምና በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል ። በጥርጣሬ ደረጃ በንክኪና በመርዝ ከተበከለ አየር የመጣ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሩ የበሽታውን ምንነት ለማረጋገጥ የደም ናሙናቸው ወደ አዲስ አበባ ተልኮ ውጤቱ እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡ በዛሬው ዕለት ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሥራ ላይ በመሆኑ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ አለመኖሩን ከወረዳው ትምህርት ቤቶች ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም