ቀጥታ፡

የጂኦሎጂካል ሰርቬይን ስራ በቴክኖሎጂ በማበልጸግ የማዕድን ዘርፉን ኢንቨስትመንት ማጎልበት ይገባል - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት  26/2012 የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይን በቴክኖሎጂ በማበልጸግ የማዕድን ዘርፉን ኢንቨስትመንት ማጎልበት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በበኩሉ መንግስት ለማዕድን ኢንቨስትመንቱ የሰጠው የትኩረት ውስንነት ዘርፉን እንዳያድግ አድርጎት ቆይቷል ብሏል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርን የ2012 ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ላለፉት 50 ዓመታት መሰረታዊ የሥነ ምድር መረጃዎችን ሲሰበስብ እንደነበር ተገልጿል።

በምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ እንዳሉት፤ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በማዕድን ዘርፍ የሚፈለገውን አገልግሎት አልሰጠም።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ተቋምን በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአሰራር ለማዘመን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ቢገልጽም እስካሁን ጠብ የሚል ውጤት አልተገኘምም ብለዋል።

ተቋሙን ካለበት ችግር ለማውጣትም የ ISO-17025 ላቦራቶሪ እውቅና ለማስገኘት በሚኒስቴሩ በኩል የሚደረገው ድጋፍም አጥጋቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የሥነ ምድር መረጃ መሰብሰብ እንዲቻልና ትንተና እንዲሰጥ ተቋሙን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እንዲከተል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ደግሞ የማዕድን ሥራ ቅንጅትን የሚፈልግ በመሆኑ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ተዋንያን ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል ወይዘሮ ፈቲያ።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የማዕድን ዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ለእቅዱ መሰረት የሚሆኑ ፕሮግራሞችን ላይ በመመስረት ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥረናል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ተቋሙ መሰረታዊ የሥነ ምድር መረጃዎችን ከመሰብሰብ ባለፈ ተንትኖ ለዘርፉ ኢንቨስትሮች በማቅረብ በኩል ውስንነት እንደነበረበት ግን አልካዱም።

መሰረታዊ የሥነ ምድር መረጃዎችን ቢሰበስብም ምን አይነት ማዕድን በምን መጠንና የት ቦታ የሚሉ መረጃዎችን ተንትኖ ማቅረብ አልቻለም ብለዋል።

በመሆኑም ተቋሙ ባለው አደረጃጀት የ ISO-17025 ላቦራቶሪም ሆነ የመረጃ ትንተና መስራት ስለማይችል በዘንድሮም ዓመት አደረጃጀት መፍጠር ትኩረታችን ሆኗል ብለዋል።

የማዕድን ዘርፉ መንግስት እንደ ጤናና ትምህርት የመሳሰሉ መስኮች ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት ሳይሆን "የውጭ ምንዛሬ ሲጎድልበት የሚያስታውሰውና የተረሳ ተቋም" እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል አልነበረውም፤ በቂ በጀት ስለማይመደብለትም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መተግበርም አልቻለም ብለዋል።

የመንግስት ቁርጠኛነት ካለ በጥቂት ዓመታ የዩኒቨርሲቲዎችን ቁጥር 42 ማድረስ አንደተቻለው ሁሉ ለኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አንድ ላቦራቶሪ መትከል አይከብድም ብለዋል።

በቀጣይም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የሰበሰባቸውን መረጃዎች በመተንተን በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች እንዲደርስ እናደርጋለን ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በተዘጋጀው አዲስ አሰራር መሰረት ብቁ የሰው ኃይል ማሟላትና ቴክኖሎጂዎችን መተግበር የቀጣይ ስራችን ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም