የመንግስት ሆደ ሠፊነት የህግ የበላይነትን በሚፈታተን ደረጃ መሆን እንደሌለበት የአፋር ህዝብ ፓርቲ ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ሆደ ሠፊነት የህግ የበላይነትን በሚፈታተን ደረጃ መሆን እንደሌለበት የአፋር ህዝብ ፓርቲ ገለፀ
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 26 ቀን 2012 የመንግስት ሆደ ሠፊነትና ከልክ ያለፈ ትዕግስተኝነት የህግ የበላይነትን በሚፈታተን ደረጃ መሆን እንደሌለበት የአፋር ህዝብ ፓርቲ /አሕፓ/ ገለፀ።
የአፋር ህዝብ ፓርቲ /አሕፓ/ የአገሪቷ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም አገሪቷ አሁን ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ መንግስት ፍትህ የማስፈን ሥራን በተገቢው መንገድ ባለመምራቱና የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አክቲቪስቶችና የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው ነው ብሏል።
የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ፣ በአገሪቷ በተጀመረው የለውጥ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዳሉ ሆነው ህግ የማስከበር ሂደት ላይ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።
በዚህ ሳቢያም በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ከዜጎች ህይወትና ንብረት ደህንነት አኳያ አስከፊ ድርጊቶች በተደጋጋሚ እየተስተዋሉ መሆኑን ገልፀው ግጭቶቹ ብሄርና ኃይማኖት ተኮር እየሆነ መምጣቱ ፓርቲውን እንዳሳሰበው ገልፀዋል።
በመሆኑም የንፁሃን ዜጎች ህይወት "ዘግናኝ በሆነ መልኩ ሲቀጠፍ ታይቷል" ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ ያለበት በመሆኑም ሆደ ሠፊነትና ከልክ ያለፈ ትዕግስተኝነት የህግ የበላይነትን በሚፈታተን መልኩ መሆን እንደማይገባ ገልፀዋል።
በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችና ለህዝብ መብት ቆመናል የሚሉ የማህበረሰብ አካላት ህግና ስርዓትን ብቻ በተከተለ ሁኔታ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው እና ህጉን ተላልፈው ሲገኙ ደግሞ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የፓርቲው የውጪ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሳ አደም በበኩላቸው መንግስት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ የማህበረሰብ አካላት የሰብዓዊ እርዳታና መልሶ የማቋቋም ስራ በአፋጣኝ መሰራት እንደሚገባው ገልፀዋል።
መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር ህገ መንግስታዊ ሥርዓትን የሚፈታተን ማንኛውንም ኃይል ለህግ ማቅረብ እንደሚገባውም ተናግረው፤ አጥፊዎችን ለህግ የማቅረቡ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ከጠብ አጫሪነት ወደ ሰላም አብሳሪነት በማደግ በኃላፊነት ስሜት ህዝቦችን የሚያቀራርቡ ዝግጅቶች፣ ዘገባዎችንና ጥንቅሮችን ማቅረብ እንደሚገባቸውም አብራርተዋል።
የአገሪቷ ህዝቦች "አገር ማለት ህዝብ ማለት" መሆኑን ተረድተው በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በመከባበር እና በመፈቃቀር የብልጽግናና የዴሞክራሲ ከፍታ ላይ እንዲደረስ የፖለቲካ አካሄዶችን በጥንቃቄ መርምሮ ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ የአብሮነት ገመዱን ማጥበቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።