ቀጥታ፡

እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዳኞች ማህበር ጋር የጠራው ስብስባ የሚካሄድበትን ቀን እስካሁን አልታወቀም

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ጋር የጠራው ስብስባ የሚካሄድበት ቀን እስካሁን አልታወቀም። ፌደሬሽኑ ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙሀን በላከው መግለጫ ከዳኞች ማህበር ጋር ነገ ስብስባ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር። የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንተርናሸናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ለኢዜአ  እንደገለጹት ማህበሩ ነገ ፌደሬሽኑ በጠራው ቀን ስብሳባውን ማካሄድ አይችልም። የስብሰባውን ጉዳይ ለመወሰን የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መሰብሰብ እንዳለበት ገልጸው አሁን የማህበሩ አባላት የሆኑ ዳኞች በየሚኖሩበት ስፍራ ስለሚገኙ ጠቅላላ ጉባኤው መሟላት እንደማይችል ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚያዚያ 29 እና 30 ቀን 2010 ዓ.ም በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ በአዳማ ስብስባ የጠራ ሲሆን በዚህ ላይም የማህበሩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መገኘት እንዳለባቸው ገልጸዋል። በተጠቀሱት ምክንያቶች ማህበሩ ከፌደሬሽኑ ጋር ስብሰባ ማድረግ የሚችለው ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሆነ ማህበሩ ዛሬ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በጻፈው ደብዳቤ ማሳወቁን ተናግረዋል። ማህበሩ ካስቀመጠው ቀን በፊት ከፌዴሬሽኑ ጋር መወያያት እንደማይችል አመልክተዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻህ በበኩላቸው ስብሰባው ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም ተካሂዶና የመፍትሔ አቅጣጫ ተቀምጦ በቀጣዩ ሳምንት ውድድር መጀመር አለበት ብለዋል። የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር መቋረጥ ክለቦችን፣ስፖርቱን አፍቃሪና አጠቃላይ እግር ኳሱን የሚጎዳ በመሆኑ ውይይቱ በአስቸኳይ ተካሂዶ ሊጉ መጀመር እንዳለበት ገልጸዋል። የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልና በዳኞች ላይ እየደረሰ ያለውን አሳሳቢ ጉዳት ለመከላከል ፌደሬሽኑ ዝግጁ እንደሆነና ማህበሩ መፍትሄ እንዲያገኙ ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ፌዴሬሽኑ ለመመለስ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። ሁለቱ አካላት ተወያይተው መፍትሔ ላይ ካልደረሱ በቀጣይ ሳምንት የሚካሄደው የ24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይካሄዱ ይችላሉ። ፌደሬሽኑ አሁን እየተከሰቱ ባሉ ችግሮች ምክንያት ዛሬና ነገ ሊካሄዱ የነበሩ የ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሌላ ጊዜ እንዲካሄዱ መወሰኑ የሚታወስ ነው። ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ ከክለቦች ጋር ባደረገው ውይይት ክለቦች ዳኞች ያቀረቡት ጥያቄ መፍትሔ አግኝቶ የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር በፍጥነት መጀመር እንዳለበት ገልጸው ነበር። የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ባወጣው ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ ዳኞች ለሶስት ሳምንት ያህል ማንኛውንም አይነት ውድድር እንደማይዳኙ መግለጻቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም