የቡና ጣዕም ውድድር መካሄዱ የቡና ዋጋን ለማስተካከል መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል....ቡና አምራች አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ጣዕም ውድድር መካሄዱ የቡና ዋጋን ለማስተካከል መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል....ቡና አምራች አርሶ አደሮች
ዲላ (ኢዜአ) ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቡና ጣዕም ውድድር መካሄዱ በየጊዜው እየቀነሰ ያለውን የቡና ዋጋ ለማስተካከል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር በጌዴኦ እና አማሮ የሚገኙ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ ከመጪው ጥር 23 እስከ 29 ቀን 2012 ዓ.ም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ አራት ማዕከላት የቡና ጣዕም ውድድር እንደሚካሄድም ተመልክቷል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ቡና አምራች አርሶ አደሮች መካከል በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ጽጌ ጅሶ አንዱ ናቸው። ውድድሩ የቡና ምርት ለማሰባሰብ በዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑ ጉድለታቸውን በማረም ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማዘጋጀት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡ በአገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቡና ጣዕም ውድድር ላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማቅረብ የአካባቢውን ቡና ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ ገልጸው፣ ውድድሩ እየወረደ ያለውን የቡና ዋጋ ለማስተካከል እንደሚጠቀም ገልጸዋል፡፡ የተፈለገውን የቡና ጥራት ደረጃ ጠብቀው በማምረትና በተባለው ጊዜ በማቅረብ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማሳየት ለሚከናወነው ሥራ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቡና ጣዕም ውድድር ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአማሮ ወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ሙሔ ጥላሁን ናቸው። የቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርታማነትን ለማሰደግ ቢደክሙም በቡና አያያዝ፣ በግብይት ሥርዓት እንዲሁም በሕገ ወጥ አሰራሮች ሲጎዱ መቆየታቸውን ነው ያስታወሱት፡፡ የቡና ጣዕም ውድድሩ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማቅረብ የአካባቢውን ቡና ከማስተዋወቅ ባለፈ እየወረዳ ያለውን ዋጋ ለማስተካከል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር እምነታቸውን ገልጸዋል። የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሪት ቅድስት ሙሉጌታ በበኩላቸው እንዳሉት ውድድሩ በዓለም ቡና አምራችና ላኪ አገራት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሲካሄድ የቆየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የቡና ሃብትና ጣዕም በጥራት በማዘጋጀት የውድድሩ አሸናፊ ብትሆን የአገሪቱን የቡና ምርት ተፈላጊነትን እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል፡፡ አስተባባሪዋ እዳሉት ውድድሩ ከጥር 25 እስከ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ሃዋሳ ከተማን ጨምሮ በ4 ማዕከላት የሚካሄድ ነው፡፡ የጌዴኦና አማሮ ቡና አምራች አርሶ አደሮች የውድድሩ ተሳታፊ በመሆን የአካባቢውን ቡና በማስተዋወቅ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የደቡብ ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ከድር በበኩላቸው የቡና ግብይት በዓለም ደረጃ ዋጋው እየወረደ መሄድ አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እንዲቀንስ አድርጓል። በዚህም አምራች አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል ባለማግኘታቸው የእርሻ መሬታቸውን ወደሌላ ምርት እንዲለውጡ እየተገደዱ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የቡና ጥራትና ምርታማነት ላይ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው የቡና ውድድር መካሄዱ አስተዋጾኦው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሬድዋን እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ተሳታፊ ለማድረግ ስለውድድሩ ደረጃዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃሰን አምቦ በበኩላቸው "አገሪቱ የብዙ ቡና ጣዕምና ዘረ-መል ባለቤት ናት" ብለዋል፡፡ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ አመራረቱን፣ ግብይቱንና የማጓጓዝ ስርዓቱን ከማዘመን ባለፈ ተፈጥሯዊ ጣዕሙን በመጠበቅ ተወዳዳሪ ለመሆን በትኩረት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።